Monday 17 November 2014

ልጅአለም።

17.11.2014 /ሲዊዘርላንድ ዙሪክ/
ኃይለመድህን አበራ
ኃይለመድህን አበራ
አንቀላፍተው ሰነባበቱ። አሁን ግን ጭር ብለዋል። ተያይዝው እቅፍቅፍ ብለው በተመሰጠ ቢጫማ ፍቅር ከደርቡ ቤታቸው ወረድ ብለው ምድር ቤት አሰኛቸውና ተያይዘው ተኙ። ….. ለኦርኬስተሩም ረፍት ስለሰጡት ውዝዋዜያቸው ሆነ ዳንሳቸው ተግ ብሏል። ጊዜያዊ ስንብት ለቋሚ ደንበኛ ኤጀንታቸው ለጌታ ንፋስ ሰጥተዋል። ከመንፈቅ በኋላ ይነቃሉ … ምንአልባት ያን ጊዜ የኢትዮጵያ ትንሳኤ ይሆን? አዎን የአውሮፓ ዕጽዋት እንቅልፍ ላይ ናቸው … ጸጥ ረጭ ብለው ሰላምን ተጎናጽፈው፣ ነፃነትን ተንትርሰው ይለሸልሻሉ … የታደሉ …
ግን ደህና ናችሁ የኔዎቹ … እኔ አይደለሁም ልጅአለም ስትል እናት ኢትዮጵያ ልዕለተ – ልዕልት ናት ለጀግንነት የጫጉላ ጊዜው ለልጇ የእትብት ልባም የሆነ ሽልማት ሥም የሰጠችው። ልጅ የተስፋ ሀገር – ጥሪት፣ የተስፋ መኖር – ትንፋሽ፣ የተስፋ ማህጸን – ታሪክ፣ የተስፋ ልዕለ – መሰረት፣ የተስፋ ላዕላዬ መዋቅር – እርገት፣ የፍጥረት ፍጹም ልዩ ሥጦታ ነው። ልጅ ፍቅርን በፍቅር ጠልፎ ሥነ ተፈጥሮን አቅልሞ፣ አለምልሞና አሳብቦ ህይወትን የሚፈወስ አንጡራ የሰማይ ጸጋ ነው። የምድርም ገነት። ልጅነት ማግኘት በራሱ ሰማያዊ ጸጋ ሲሆን እናትነት ማግኘትም ሰማያዊ – ሥጦታ።
ዬልጅነት የከበረ ጸጋነት ማረጋገጫው ደግሞ ተግባሩ ነው። ተግባሩም ግልብ ሳይሆን ዬእትብትን ውስጥ ባግባቡ የሚተረጉም ልዩ ክህሎት ነው። ክህሎቱ በሰው ሰራሽ ስልጠና የሚገኝ አይደለም። ይልቁንም ከሰጪው የተበረከተ ፍጹም ረድኤት እንጂ። የእናትና የልጅ ግንኙነት ሁነት ቢሆን ኮርስ የሚወሰድበት፣ ተቋም ተከፍቶ፣ ሰራዊት ተሰማርቶ በገሃዱ አለም ታሪክ የሚንቦለቦል ወይንም የሚጠፈጠፍ አይደለም። የቅድስና መርሃዊ ክንዋኔው ኤዶማዊ ነው። ጠረኑም ሰውኛ አይደለም አምላካዊ
እንሆ ዬታላቅ ሀገር ኢትዮጵያ ልጆች ዘመንና ወቅት ሳይገድባቸው ወይንም ደንበር ሳይወስናቸው የእናታቸውን ዘመነ ህማማታዊ ጥሪ በተግባር አብተው አለሁባይነትን ዘውድ እንዲደፋ እንዲህ ይፈቅዱለታል። በሥርዓተ ንግሥናው ቅብዕ ልጅነት የሚከውኑት ገድል ደግሞ መስዋዕትነትን ፈቅደውና ወደው ደስ ብሏቸው በማጽደቅ ነው።
ዬጡትነት ውለታዊ ኪዳን ፍሬ ነገሩ በመሆን ተራምዶ፣ በውስጡ በመኖር በድል አድራጊነት ያበራል። ዘመኑ ሁኗል የዕዬለቱ የጀግና ፍጥረተ ነገርን የማዬት። ዳር ድንበሩ – ጫካ ዱሩና ገደሉ፤ በወርቃማ ሸንተረራማዋ ባዕት ብቻ ሳይሆን በሰለጠነው ዓለም ሳይቀር ኢትዮጵያዊ ጀግንነት ቦግ ብሎ በርቶ እዬታዬ ነው። የትናንቱ የእነ አብዲሳ አጋ፤ ዘራዕይ ደረስ፣ በላይ ዘለቀ፣ ሞገስ አስገዶምና አብርኃም ደቦጭ፤ የነመንግሥቱ ንዋይ የነሳራ ግዛውና የሌሎችም ገድላት ታሪክን ትውልዱ አንግሦ በውደሳ ብቻ ሳይታቀብ እንሆ በዓለም ሁሉ ያሉ ተተኪዎችን በጀግንነት ክታብ ተግባራቸው አንቱ አስኝቷቸዋል። ዓይናችንም በጀግንነት መስኖ በዬመስኩ እያለሙት ይገኛሉ –  አርበኞቻችን። ኑሩልን። ፈጣሪ አማላካችንም ይጠብቅልን። አሜን!
ኢትዮጵውያን በዬትኛውም ዓለም ከሀገር እርቀውም ሆነ እዛው ይኑሩ ደማቸውን ገላጭ የሆነውን የአርበኝነት ትውፊተ – አደራቸውን ሳያሾልኩ ወይንም ሳይጨፈልቁ በተግባር ያንቆጠቆጡበት ምዕተ ዓመት ማለት ይቻላል – 21ኛው ክፍለ ዘመን። በዬትኛውም ሙያ፤ በዬትኛውም ዕድሜ፤ በዬትኛውም የዕውቀት ደረጃ ይገኙ በተገኘው ክፍተት ሁሉ ስለ አረንጓዴው ቢጫ ቀዩ ዘመን አሻጋሪና ትውልድን ገንቢ እንዲሁም ነገን አሳዳሪና መሪ ሰንደቃቸው ግንባራቸውን ሳያጥፉ፤ ፊት ለፊት ወጥተው የመስዋዕትነትን ጽዋ በሐሴት እዬተቀበሉ ይገኛሉ። ማገዶነታቸውንም – አስመችተውታል።የታደሉ!
ሌት ተቀን ደከመን ሰለቸን ሳይሉ ባንዳን በማጋለጥ፤ ባዕድ ስሜትን እርቃኑን በማስቀረት፤ መረጃ በማለዋወጥ፤ ወቅታዊ ሁኔታዎችን በማቀባበል፤ በተገኙ አለምአቀፍ መድረኮች ሁሉ የትናንት አርበኝነት ታሪካቸውን በበራ አዲስ ታሪክ እንሆ ያንቆጠቁጡታል። ያሳምሩታል። ያስውቡታል። ከጽንፍ እስከጽንፍ ለሰንደቃቸው “የቤትህ ቅናት በለኝ” ያለውን የልብአምላክ ዳዊት ምስብዕክ ያመሳጥሩታል። እነኝህ የተግባር ቀንዲሎቻችን፣ የአንድምታ ትውፊትነት ከደማቸው ያገኙት ሲሆን የሰውነታቸው ልዩ ህዋሳዊ ንጥረ ነገር ነውና ሁነውበታል።
ጀግኖች የትም ቦታ፤ በዬትም ሁኔታ፤ በማናቸውም ጊዜ ይፈጠራሉ። እንሆ የካቲት 17 ቀን 2014 እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በግልጽና በስውር በተገኘው አሳቻ ጊዜ በሽፍታው ወያኔ ለሚታረዱት ወገኖቹ በልበ ሙሉነት ጥቃትን በድል ያወራረደው ቀንበጥ ጀግና ካፒቴን አበራ ሃይለመድህ የተፈጠረውም በዘመናችን ነው። ጀግንነትን ካለግድፈት አዬር ላይ ነፍስ ዘርቶ አብቅሎ ያሰበለ – አባወራ። ልጅአለም ብርሃናማው ሞገዱ ዓለምን አካቶ አነጋነገ። እናቱ አንተ አለሜ፣ ልጄ ለምለሜ ብላ በጠራቸው ጊዜ ቀድሞ ጥቋቷን ከቶውንም ጥበቡን ተማራምሮ ሊደርሱበት በማይችሉት ፍጹም ረቂቅ ብልህ ክንዋኔ በድል አኩርቶ ከወነው። የሰማዕቱ አሰፋ ማሩ የጠራራ ጸሐይ መስዋዕትነት ሆነ የሌሎች ቅን ወገኖች ወጥቶ ቀሪነት ጥቃት ካለ ሠራዊት ሰልፍ፤ ካለ ከባድ መሳሪያ ትርምስ ጸጥ ባለው ባዘቶ ላይ በጣሊያንና በፈረንሳይ አውሮፕላን በክብር ታጅቦ ትልሙን ሲዊዘርላንድ ጄኔባ ላይ ሰፈፉን በድል መና ከተበ። ተባርክ የእኔ ጀግና! አሳዳጊህንም ብርክ – ቅድስ – ጥብቅ! ያድርግ የዕንባ አምላክ …. የምጡን የቀለበት ዘመንም ይፍታህ ይበለው። አሜን።
የልጅአለሙ – የደማሙ
ውሉ ሰማይ ላይ ሆኖ ማማሩ፤
የጉልህ መንበሩ ገበሩ፣
የምርጥ – ዘሩ!
የመድህን ሰፋኒተ – ሥራ
ሃይሉነን ከብብክቦ አፈራ።
ፍቅር ትርጉሙ – ድሩ
የሰማይ ታምር ውቅሩ፤
ድል ሆነለት አዳሩ፣
የጀግና ውሉ ሥሩ
ትሩፋተ – ደንበሩ!

1 comment:

  1. የመድኃኒት ንግድ ሥራዬን ለማስፋፋት በተጠቀምኩበት ብድር ለመርዳት ሚስተር ቤንጃን ከሚያስፈልጓቸው በላይ አልፈዋል ፡፡
    እነሱ ለመስራት ወዳጃዊ ፣ ባለሙያ እና ፍጹም ዕንቁዎች ነበሩ ፡፡ እኔ ለማነጋገር ብድር የሚፈልግን ማንኛውንም ሰው እመክራለሁ ፡፡ Lfdsloans@outlook.com.WhatsApp ... +19893943740.

    ReplyDelete