Wednesday 12 November 2014

.እንግሊዝ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን በተመለከተ ደብዳቤ መጻፏን ሚኒስትር ሬድዋን አረጋገጡ

- በመጪው ምርጫ የውጭ ታዛቢዎች እንደሚኖሩ ገለጹ -የኃይል መቆራረጥ እንደሚያጋጥም በቅድሚያ አለመነገሩ ስህተት መሆኑን ገለጹ
የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን በተመለከተ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደብዳቤ መጻፋቸውንና ኢትዮጵያም አቋሟን ግልጽ ማድረጓን የመንግሥት ጉዳዮች ኮሙዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ሚኒስትሩ አቶ ሬድዋን ሁሴን ገለጹ፡፡
ሚኒስትሩ አቶ ሬድዋን በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ማክሰኞ በሰጡት መግለጫ፣ ዴቪድ ካሜሩን ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደብዳቤ መጻፋቸውን የተለያዩ የውጭ ሚዲያዎች መዘገባቸውን በተመለከተ ማረጋገጫ እንደሰጡ ተጠይቀዋል፡፡ ‹‹ለምን ጻፉ ማለት አይቻልም፡፡ ምን መለሳችሁ ነው የሚጠየቀው፤›› በማለት ሚኒስትሩ አቶ ሬድዋን አረጋግጠዋል፡፡
 በሪፖርተር/ናሆም ተስፋዬ ዋና ዜና
የተለያዩ የእንግሊዝ ሚዲያዎች ኢትዮጵያ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ላይ ቀደም ሲል የተፈረደውን የሞት ቅጣት እንዳትተገብር እንዲሁም ኢትዮጵያ ለሚገኘው የእንግሊዝ ኤምባሲ አቶ አንዳርጋቸውን የመጐብኘት ቋሚ ፈቃድ እንዲሰጥ በደብዳቤያቸው መጠየቃቸውን ዘግበዋል፡፡
ለዴቪድ ካሜሮን ደብዳቤ መልስ መሰጠቱን ያረጋገጡት አቶ ሬድዋን፣ ‹‹በተጨባጭ የተፈረደበትን ግለሰብ ነው የያዝነው፤ እንዲህ ብታደርጉት ባታደርጉት ብሎ ማንሳት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም እነሱም የሚመለከታቸው በመሆኑ፡፡ በዚህ ምክንያት ግን የእኛ መልስ በራሳችን ሕግ መሠረት ዓለም አቀፍ ሕጉም በሚለው መሠረት የምናደርገውን እናደርጋለን፤›› ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የምትተገብረው የራሷን ሕግ መሆኑን የገለጹት አቶ ሬድዋን፣ ‹‹ከነጭም ከጥቁርም የሚመጣን ደብዳቤ ተንተርሰን ምንም አንተገብርም፤›› ብለዋል፡፡
‹‹እነሱ ዜጋዬ ነው ብለዋል፤ የእነሱ ዜጋ እንደ ቼ ጉቬራ ነፃ አውጣ ተብሎ ኢትዮጵያ ውስጥ አልተላከም፡፡ የእነሱ ዜጋ ከነበረ የእንግሊዝ ዴሞክራሲ ይበልጥ ለመጨመር መታገል ይችል ነበር፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያ በቅጥር ነብሰ ገዳይነት ካልተሰማራ በስተቀር ሌላ ሚና አልነበረውም፤›› ብለዋል፡፡
በማከልም ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን ደብዳቤ ጽፈው፣ በኢትዮጵያ በኩልም መልስ መሰጠቱን አስታውሰው፣ በደብዳቤው የቀረቡ ጥያቄዎች ቅሬታ እንዳላስነሱ ሁሉ መልሱም ቅሬታ አያስነሳም የሚል ተስፋ በኢትዮጵያ በኩል መኖሩን ተናግረዋል፡፡
በቀጣዩ ምርጫ የውጭ ታዛቢዎች በመንግሥት ግብዣ እንዲሁም የታዛቢዎች ጥያቄ ላይ ተንተርሶ እንደሚፈቀድም ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ከዚህ ቀደም እንደነበሩት ሁለት ምርጫዎች ‹‹መዘውሩን ይዘው አገሪቱን መምራት የሚፈልጉ ታዛቢዎችን›› መንግሥት እንደማይጋብዝ አመልክተዋል፡፡
ሰሞኑን ባልተለመደ መልኩ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚስተዋለው የኃይል መቆራረጥ ኅብረተሰቡን እንዳስከፋና መንግሥት ቀድሞ ችግሩን በመናገር ኅብረተሰቡን ዝግጁ አለማድረጉ የኃላፊነት ጉድለት መሆኑን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄም፣ ቀድሞ የማሳወቁ ሥራ ለመሥራት እንደተሞከረ፣ ነገር ግን ውስን እንደነበርና ይህም እንደ ስህተት እንደሚቀበሉት ተናግረዋል፡፡ በጣና በለስ ማሠራጫ ጣቢያ በተፈጠረ የባትሪ ችግር የኃይል መቆራረጡ መከሰቱን በአሁኑ ወቅት ግን ችግሩ መቀረፉን ተናግረዋል፡፡
አጠቃላይ የኃይል መቆራረጥ ችግር ደግሞ ከማሠራጫ መስመሮች አቅም ማነስ ጋር የተያያዘ እንደሆነና በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ይፈታል ተብሎ እንደሚገመት ተናግረዋል፡፡

No comments:

Post a Comment