Sunday 16 November 2014

ጋዜጠኞችና ጦማሪያን ከተመሠረቱባቸው ሁለት ክሶች አንዱ ተሰርዞ ሌላው እንዲሻሻል ትዕዛዝ ተሰጠ

በማረሚያ ቤት የተጠርጣሪዎች አያያዝ ጉዳይ አሁንም መፍትሔ አላገኘም
በሽብርተኝነት ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸው ጋዜጠኞችና ጦማሪያን የተመሠረተባቸውን ክስ ተቃውመው ባቀረቡት መቃወሚያ መሠረት፣ ቀርበውባቸው ከነበሩት ሁለት ክሶች አንዱ ሙሉ በሙሉ ተሰርዞ ሌላኛው እንዲሻሻል ፍርድ ቤት ኅዳር 3 ቀን 2007 ዓ.ም. ትዕዛዝ ሰጠ፡፡
የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ የመሠረተውን ክስ በመርመር ላይ ለሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት፣ የተመሠረተባቸውን ክስ የተቃወሙት ጋዜጠኞች ተስፋለም ወልደየስና አስማማው ኃይለ ጊዮርጊስ እንዲሁም ጦማሪያን፣ ማኅሌት ፋንታሁን፣ ኤዶም ካሣዬ፣ ዘላለም ክብረት፣ አቤል ዋበላ፣ ናትናኤል ፈለቀና አጥናፍ ብርሃኔ ናቸው፡፡
ዓቃቤ ሕግ በመሠረተው ክስ ተጠርጣሪዎቹ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1ሀናለ)፣ 38(1እና2)ን እንዲሁም የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 4ን መተላለፋቸውን በክሱ አስፍሯል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ከላይ የተጠቀሱትን የሕግ አንቀጾች በመተላለፍ የሽብርተኝነት ወንጀል ለመፈጸም ‹‹አቅደዋል፣ ተዘጋጅተዋል፣ አሲረዋልና አነሳስተዋል›› ማለቱን ክሱ ይገልጻል፡፡ እንዲሁም በወንጀል ሕጉ፣ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በሁከትና በአመጽ ለመለወጥ በማሰባቸው በዋና ወንጀል አድራጊነት፣ ሕገ መንግሥቱንና በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ላይ በሚደረግ የሙከራ ወንጀል በሚል የቀረበባቸውን ክስ ተቃውመዋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በጠበቆቻቸው አቶ አምሃ መኰንንና በአቶ ሽብሩ በለጠ አማካይነት ባቀረቡት የክስ መቃወሚያ እንዳብራሩት፣ በወንጀል መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 112 መሠረት የቀረበባቸው ክስ፣ ዓቃቤ ሕግ ተፈጸመ ካለው ድርጊትና ከጠቀሰው ሕግ ጋር የተቀራረበ አለመሆኑን በዝርዝር አስረድተው ነበር፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ፈጽመዋቸዋል ተብሎ በክሱ ዝርዝር የተመለከቱት ተግባራት፣ በሕግ የተፈቀዱና ሕገ መንግሥታዊ ጥበቃም የተደረገባቸው፣ ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ከመሆናቸውም በተጨማሪ የወንጀል ኃላፊነትን የማያስከትሉ ስለመሆናቸው በወንጀል መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 2 እና በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 26፣ 29 እና 31 ላይ መደንገጋቸውን አስረድተዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ የቀረበባቸው ክስ ግልጽ ስላልሆነና የሚከላከሉበትን ጉዳይ ለይተው፣ አውቀውና ተረድተው ለመከላከል እንደማይችሉ በመቃወሚያቸው በዝርዝር ጠቁመው፣ በተቃወሙት መሠረት ፍርድ ቤቱ ክሱን፣ መቃወሚያውንና የዓቃቤ ሕግን መልስ መርምሮ፣ የተጠርጣሪዎቹን ተቃውሞ በመቀበል ዓቃቤ ሕግ ክሱን እንዲያሻሽል ብይን ሰጥቷል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በቡድንና በድርጅት ውስጥ የሽብርተኝነት ተሳትፎ እንዳላቸው በዓቃቤ ሕግ ክስ ላይ መጠቀሱን ተከትሎ፣ እነሱን ይሁን ወይም እነሱ አደራጇቸው የተባሉትን በሚመለከት በግልጽ አለመቀመጡን በመዘርዘር ተቃውሞ አቅርበዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ በክሱ ውስጥ እንዳብራራው ተጠርጣሪዎቹ የሥራ ክፍፍል ማድረጋቸውን የጠቀሰ ቢሆንም፣ ማን በምን ሥራ ላይ እንደተሰማራ በግልጽ ተለይቶ አለመቀመጡንም በክስ መቃወሚያቸው አካተው አቅርበዋል፡፡
ሥልጠናዎችን በመውሰድና በመሠልጠን የሚለው ክስም፣ ሥልጠናው የትና መቼ እንደተወሰደ፣ ሥልጠናውን ያዘጋጀው ማን እንደሆነና የሥልጠናው ርዕስ ምን እንደሆነ በግልጽ ተብራርቶ ባለመቅረቡ፣ የመከላከል መብታቸውን እንደሚያጣብብም በመቃወሚያቸው አመልክተዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ከላይ በተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች የቀረቡትን የመቃወሚያ ነጥቦች ከሕጉ ጋር በማገናዘብ መመርመሩን አስታውቆ፣ የተጠርጣሪዎቹን የክስ መቃወሚያ በመቀበል ዓቃቤ ሕግ ክሱን እንዲያሻሽል አዟል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ለኢሳት ሬዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያ ሪፖርት አድርገው፣ ህቡዕ ቡድኑ ድጋፍ እንዲያገኝ ማድረጋቸውን በሚመለከት ዓቃቤ ሕግ በዝርዝር ያቀረበውን ክስ የተቃወሙ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ በቀጣይ በማስረጃ እንደሚጣራ በመግለጽ ተቃውሞአቸውን ውድቅ አድርጐታል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ወስደዋቸዋል የተባሉት ሥልጠናዎችና ለመገናኛ ብዙኃን መረጃ ማስተላለፋቸው ወንጀል ስላለመሆኑ ተጠርጣሪዎቹ ያቀረቡትን ተቃውሞም ፍርድ ቤቱ አልተቀበለውም፡፡ ዓቃቤ ሕግ በክሱ ተጠርጣሪዎቹን የሽብር ቡድን አባል እያለ ያቀረበው ክስ አዋጁንና ሕገ መንግሥቱን የጣሰ ስለመሆኑ በመቃወም ያቀረቡትን መቃወሚያም ፍርድ ቤቱ አልተቀበለውም፡፡
ዓቃቤ ሕግ ተጠርጣሪዎቹን ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለማፍረስ ‹‹በማሰብ›› በሚል ያቀረበውን ክስ፣ ተጠርጣሪዎቹ ‹‹ማሰብ አያስከስስም፣ አያስቀጣምም›› በማለት ክሱ እንዲሰረዝ ባቀረቡት መቃወሚያ መሠረት ክሱ እንዲሰረዝ አዟል፡፡
ፍርድ ቤቱ ከላይ የተጠቀሱትን ብይኖች ሰጥቶ፣ ዓቃቤ ሕግ ክሱን አሻሽሎ እንዲያቀርብ ለኅዳር 24 ቀን 2007 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ሴት ጦማሪያን ቀደም ባሉት ቀጠሮዎች፣ በማረሚያ ቤት ያለባቸውን የአያያዝ ችግር በሚመለከት ባቀረቡት አቤቱታ መሠረት፣ የማረሚያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ቀርበው እንዲያስረዱ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ያስተላለፈ ቢሆንም፣ ዋና ዳይሬክተሩ በሥራ ምክንያት እንዳልቀረቡ ተገልጾ ተወካይ ቀርበው አስረድተዋል፡፡
በማረሚያ ቤቱ የሕግ አገልግሎት ማስተባበሪያ ኃላፊ መሆናቸውን የገለጹት ተወካዩ ለፍርድ ቤቱ ደብዳቤ ያቀረቡ ሲሆን፣ የደብዳቤው ይዘት በጦማሪያኑ ላይ ምንም ዓይነት መድሎም ሆነ እነሱን የሚያገል ነገር እንደሌለ እንደሚገልጽ ፍርድ ቤቱ ለታዳሚው ተናግሯል፡፡
ከሰኞ እስከ ዓርብ ሙሉ ቀንና ቅዳሜና እሑድ ግማሽ ቀን ማረሚያ ቤቱ ለጠያቂ ከፍት መሆኑን ያስረዱት ተወካዩ፣ በማረሚያ ቤቱ ደንብና ሥርዓት መሠረት ሁሉም እኩል እየተስተናገደ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የተወካዩ ምላሽ ያልተዋጣላቸው ተጠርጣሪዎቹ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ እንኳን ሊሻሻል ቀርቶ እንዲያውም ቤተሰቦቻቸውን እንዳስፈራሯቸው አስረድተዋል፡፡ ፍርድ ቤት በሰጠው ትዕዛዝ መሠረት የሚፈጸም መስሏቸው ቤተሰቦቻቸው እንደማንኛውም ጠያቂ ከጠዋቱ አራት ሰዓት በማረሚያ ቤቱ የደረሱ ቢሆንም፣ ‹‹ማን በዚህ ሰዓት ኑ አላችሁ?›› በማለት ቁጣ እንደደረሰባቸው አስረድተዋል፡፡
ተወካዩ ግን፣ ተጠርጣሪዎቹ ያሉትን ነገር እንዳልሰሙና ለአስተዳደሩም እንዳልደረሰው በመናገር፣ በደል ያደረሰባቸውን አካል በስም ይዘው ቢናገሩ፣ ማረሚያ ቤቱ ዕርምጃ እንደሚወስድ ገልጸዋል፡፡ የተወሰነ የሰው ኃይል ስላለ ሁሉንም ለማዳረስ ሲሠራ የተወሰነ አለመግባባት ሊፈጠር እንደሚችል ተወካዩ ሲናገሩ፣ ፍርድ ቤቱ በመሀል ገብቶ ‹‹ስንት ሴት ተራሚዎች አሉ?›› የሚል ጥያቄ ሲያቀርብላፀቸው ‹‹ከ500 እስከ 600 ይደርሳሉ›› ብለዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ የመጨረሻ ዕድል ለማረሚያ ቤቱ መስጠቱን ተናግሮ በቀጣይ ቀጠሮ የማይስተካከል ከሆነ ማስረጃ ሰምቶ ዕርምጃ እንደሚወሰድ ለተወካዩ አስረድቷል፡፡

No comments:

Post a Comment