Monday 16 March 2015

ኢዶሳ አ. ቱፋ:- ከንቲባው

በኢዶሳ አ. ቱፋ
ክፍል 1
የበሉት ምሳ በወጉ ሳይወራረድላቸው፣ የተጎነጩት የወይን ጠጅ ቃናው ከአፋቸው ሳይጠፋ፣ አንገታቸውን የሚተናነቅ፤ የህይወት ጥያቄ የሚያጭር ፈተና ድቅን አለባቸው። ጉዳዩ አዲስ ባይሆንም፣ ወትሮ በአደባባይ አልነበረም። ዛሬ ግን በግላጭ እነዚያ ወገኖቻቸው በሚሰሙበት ሁኔታ የውርደት ማቃቸውን ተከናነቡት። ከንቲባው ተሰደቡ፣ በአደባባይ።
«ከርፋፋ የከተማ አስተዳዳሪዎች» አሏቸው አለቃቸው፤ አዛዥ ገዢያቸው፣ ቁልቁል እየተመለከቱ ።
በርግጥ የእነ-እንትና ካድሬዎች በሙሉ አለቆቻቸው ማን እንደሆኑ ዘንግተው አያውቁም። በደብዳቤ፣ በስልክ፣ በአካል በተገናኙ ሁሉ አዛዦቻቸው ስፍር ቁጥር የላቸውም። አንዳንዴማ ከሚያዙት፣ የሚያዛቸው የሚበልጥ ይመስላቸዋል። ታድያ ያን፣ ሁሉ «ሰሚ የለውም» እያሉ፣ ዋጥ አድርገው ሲያልፉት ኖረዋል።
ከንቲባው መተንፈስ እስኪሳናቸው በጭንቀት ተዋጡ። ትንሽ ቢያስነጥሱ አለቃቸው ቅጽበታው እርምጃ በመውሰድ «ልክ እንዳያስገቧቸው» በእጅጉ ሰጉ።
ሞቃታማው የአዋሳ አየር ታክሎበት፣ ሆዳቸው ተላወሰ።
«ግን» አሉ ከንቲባው፣ «እነዚያ ጥቂት ጠባቦች ከውጭ ሆነው ቢንጫጩ፣ ምን ያመጣሉ?! እዚህ ላሉትማ፣ ከበቂ በላይ ዝግጅት አለን» ሲሉ፣ ከዚህ ቀደም የከተማው የደህንነት ሃላፊ ደጋግሞ የነገራቸውን አስታወሱ። የአለቃቸውን የትምክህት ድንፋት እንኳን መከታተል ተሳናቸው። እንዴት በከተማው ሊነሱ የሚችሉ ተቃውሞዎችን በአጭር መቅጨት እንደሚቻል፣ ብቻቸውን ማሰላሰል ተያያዙት።
የተላለፈላቸውን መመርያ ያለ አንዳች ማመንታት ከማስፈጸም ውጭ አንዳች አማራጭ እንደሌላቸው ለራሳቸው እርግጠኛ ሆኑ። የህይወት ገመዳቸው እንዳትበጠስ የመጨረሻውን ጥንቃቄ መውሰድ እንዳለባቸውም በቅጽበት አሰቡ። «እናስ ከእንግድህ አንዳች ማመንታት አያዋጣም። ምን ላድርግ?» ስሉ ራሳቸውን ጠየቁ።
የኦሮሚያውን ፕሬዝዳንት በአይን ፈለጉት። በእረፍት ሰዓት አግኝተውት፣ ሊያማክሩት አሰቡ። «ራሴን ለማውጣት፣ እሱ የፊንፊኔ ልዩ ዞን መሪዎችን ሰብስቦ እንዲገመግምና ቢያንስ ገሚሱን እንዲያባርር እመክረዋለሁ። ይህ ደግሞ፣ ለኔም ለሱም ጥሩ ማምለጫ ነው። እነሱ ናቸው ከርፋፎች። የተላለፈላቸውን መመርያ አስፈጽመው ቢሆን ኖሮ፣ ዛሬ ጉዳችን አደባባይ ባልወጣ ነበር። ደግሞ፣ እዚህ ውስጥ ስንት አድር-ባይ አለ። አሁን ሳይመሽ ነው ወሬውን በዓለም የሚያደርሱት» አሉ ከንቲባው ራሳቸውን እስኪስቱ በሃሳብ እየተናወጡ።
የአለቃቸው የእብሪት ንግግር ደጋግሞ ከጆሯቸው ውስጥ አቃጨለ።
«ልክ እናስገባቸዋለ!»
«በርግጥ እነዚህ ሰዎች እኮ ጨካኞች ናቸው፤ አይምሩንም» ሲሉ ልሏ ልባቸው ከመቅጽበት መቶ መምታት ጀመረች።
«ደግሞስ ያሻቸውን ቢያደርጉን የሚሳለቅብን እንጂ የሚያዝንልን የት አለና?» ሲሉ ራሳቸውን ጠየቁ። «በቃ አሁን ያለው አማራጭ ልክ እንደ-ከዚህ ቀደሙ የበታች ተሿሚዎችን በደካማነት በመፈረጅ ማባረር አልያም መቅጣት ነው። ያኔ፣ አለቆቻችን ንዴታቸውም በከፊልም ቢሆን ይረግባል። ከዚያን አዳዲስ ሰዎችን በየቦታው በመሰግሰግ በአዲስ ጉልበት መመሪያውን ማስፈጸም ነው። ሽብርተኞችንም መቅጣት ነው። ልክ ማስገባት ነው!» አሉ እሳቸውም በተራቸው።
ለካስ ሳያስቡት «ልክ ማስገባት ነው!» የሚለው ሃረግ ከአፋቸው አፈትልኮ ከግራና ቀኝ ጎናቸው የተቀመጡት ሹማምንት ጆሮ ገባ። አንደኛው በለበጣ ሳቅ ሲያዩአቸው ሌላኛው ግን ልክ በሚያስገባ ግልምጫ ገላመጧቸው። ከንቲባው በእጅጉ ደነገጡ።
ማምለጫ ፍለጋ፣ የጭንቀታቸውን «እውነታቸውን ነው» ሲሉ፣ የአለቃቸውን ንግግር የሚደግፍ ድምጽ አሰሙ። «እነዚያ የልዩ ዞን አመራሮች ላይ የማያዳግም እርምጃ መወሰድ አለበት» ሲሉ ከጎናቸው የተቀመጡትን ሹማምንት ሰይጣናዊ እሳቤ አቅጣጫ የሚያስቀይስ ቃል ወረወሩ።
በውስጣቸው ግን «የተናገርኩት ቃል ያስገመግመኝ ይሆን?» ሲሉ አሰቡ።
እየተሰደቡና እየተቀጡ የተማሩትን አማሪኛ ብቸኛ ቋንቋቸው ካደረጉት ዓመታት አስቆጥረዋል። ንግግራቸውን ለማሳመርና ማንነታቸውን እንዳያሳብቅ ለማድረግ ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርጉ ኖረዋል። ይህ ደግሞ ለሹመትና ለተሻለ ኑሮ ቁልፍ ጉድይ መሆኑን ጠንቅቀው ያምኑበታል። በቋንቋው ጉዳይ ውስጣቸው ደስታኛ ሆኖ ባያውቅም፣ አንደበታቸው ግን አንድም ቀን ተከፋሁ ብሎ አያውቅም።
«ስሰደብ ተምሬው፣ ዛሬም እሰደብበታለሁ» አሉ ለራሳቸው። ላለመሰደብ ግን ምን ማድረግ እንዳለባቸው የሚነግራቸውን ህሊና ማግኘት አልቻሉም።
በሁኔታቸው ደንግጠው ሃሳባቸውን ለማሰባበብ ሞከሩ። አለቃቸው ድንፋታቸውን ቀጥለዋል።
«ማስተር ፕላኑ በምንም መልኩ ተፈጻሚ ይሆናል!» ሲሉ ሰሟቸው።
«በቃ፣ ፊንፊኔ ልዩ ዞን አዲስ አበባ ስር ትገባለች። እኔም ጥርሴን ነክሼ እቅዱን ካስፈጸምኩ የትልቋ አዲስ አበባ ከንቲባ ሆኜ እቀጥላለሁ። በቃ፣ ምን ይመጣል፣ እንዲሁ ይንጫጫሉ እንጂ፣ ምንም አያመጡም» ሲሉ በውጪ የሚኖሩትን ‘አሸባሪዎች’ ዳግም አስታወሱ።
ከቲባው የአለቃቸውን ንግግር በመደገፍ ተጨማሪ ሃሳብ ለማከልና ለማስተር ፕላኑ ተፈጻሚነት ጽኑ አቋም እንዳላቸው፣ በዚህ አጋጣሚ ለማረጋገጥ የማስታወሻ ደብተራቸውን እያገላበጡ መጻፍ ጀመሩ። መወሰድ ያለባቸውንም እርምጃዎች በቅደም ተከተል ደረደሩ።
- በአስቸኳይ ጸረ-ማስተር ፕላን የከተማ አመራሮችን ገምግመው ማንሳትና በቆራጥ አመራሮች መተካት፤
– መነሳት የሚገባቸውን አርሶ አደሮች መለየትና ያለ አንዳች ማመንታት ቦታውን ማስለቀቅ፤
– መሬት የሚፈልጉ የልምዓት አጋር የሆኑትን የሃገር ውስጥና የውጭ ሀገር ባለ-ሃብቶችን ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት መሬቱን መደልደል፤
– በሃገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱትን የልምዓት ጸሮች ልክ ማስገባት፤
– በውጭ ያሉትን ደግሞ በተቻለ መጠን እያደራጁ መሬት በመስጠት የልምዓት አጋር ማድረግ፤
– ከዚህ የሚያፈነግጡትን በቅርበት መከታተልና እንቅስቃሴያቸውን መግታት፤ ወዘተ …
ሲሉ ሃሳባቸውን በልበ-ሙሉነት ለማቅረብ ተዘጋጁ። የአለቃቸውን ይሁንታ ለማግኘት፣ ምንም ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ወሰኑ።
ከንቲባው የአለቃቸውን የእብሪት ንግግር ፍጻሜ ተከትለው ብድግ አሉ። ላይ በላይ እየተነፈሱ፣ የጻፉትን አነበቡ። ድምጻቸው በሳግ ተቆራረጠ። ፊታቸው በላብ ተጠመቀ። አለቃቸው ላስተላለፉት መሪ ቃል፣ በከተማው መስተዳድር ስም ደጋግመው አመሰገኑ።
የተወሰኑ ተሰብሳቢዎች የወጉን አጨበጨቡላቸው። አለቃቸው ግን እንኳን ሊያጨበጭቡ ቀና ብለውም አሏዩአችውም።
ከንቲባው ለአንድ አፍታ ወደ ተሰብሳቢው ፊታቸውን አዞሩ። ከሺህ በላይ አይኖች በትንግርት ሲያዩአቸው ተመለከቱ።
«አንተ ውሸታም፤ አንተ አድር-ባይ፤ አንተ ፈሪ፤ አንተ የገበሬ ማሳ ቸርቻሪ» የሚሏቸውን ያክል ተሰማቸው። ደነገጡ። እግሮቻቸው ብርክ እየመቱ ቁጭ አሉ።
«ጽቡቅ እዩ» አላቸው ከቀኝ ጎናቸው ተቀምጦ የነበረው ተሰብሳቢ።
ቀደም ስል በገላመጣቸው ጊዜ «በቃ ያስገመግመኛል» ብለው ፈርተውት ነበር። አሁን ሃሳባቸውን በመደገፉ ደስ አላቸው። አመሰገኑት። እሱም አለቃቸው ነው። ከንቲባው ከሚቆጥሩት በላይ አለቆች አሏቸው። ምን ገዷቸው ለሁሉም ይታዘዛሉ። ለሁሉም መሬት ያድላሉ። እድሜ ለኦሮሞ ማሳ። ከልካይ የለሌበት።

No comments:

Post a Comment