Friday 19 December 2014

በነአብርሃ ደስታ ላይ ለታህሳስ 15 ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠ ∙ ተከሳሾቹ የክስ መቃወሚያ አቅርበዋል

በእነ ዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ የሚገኙት የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮችን ጨምሮ 10ሩም ተከሳሾች ለታህሳስ 15 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
Habtamu abrhayeshiwas daniel
ዛሬ ታህሳስ 9 ቀን 2007 ዓ.ም በፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ 19ኛው ወንጀል ምድብ ችሎት የቀረቡት የሰማያዊ፣ የአንድነትና የአረና ፓርቲዎች አመራሮች የሆኑት አቶ የሺዋስ አሰፋ፣ አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ አቶ ዳንኤል ሺበሺ እና አቶ አብርሃ ደስታ እንዲሁም አንደኛ ተከሳሽን ጨምሮ ስድስት ተከሳሾች በጠበቆቻቸው አማካኝነት የክስ መቃወሚያቸውን ይዘው ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡
ሆኖም ግን 7ተኛ ተከሳሽ አቶ አብርሃም ሰለሞን የሰጠው የተከሳሽነት ቃል ከክሱ ጋር ተያይዞ ለጠበቃው አለመቅረቡን ተከትሎ ጠበቃው የክስ መቃወሚያ ለማዘጋጀት ባለመቻላቸው የተከሳሽ ቃልን የያዘውን ዶክሜንት ከጽ/ቤት ወስደው መቃወሚያቸውን እንዲያስገቡ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡
በዚህም መሰረት ፍርድ ቤቱ የተከሳሾችን የክስ መቃወሚያ መርምሮ ብይን ለመስጠት ለታህሳስ 15 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
በሌላ በኩል ተከሳሾች በእስር ላይ ባሉበት ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ሊጎበኟቸው የሚሄዱ ቤተሰቦቻቸውና ወዳጆቻቸው ወደ እስር ቤቱ ሲገቡ በተለየ መዝገብ እንዲመዘገቡ እየተደረጉ መሆናቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡ ተከሳሾች ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት ቤተሰቦቻቸውና ወዳጆቻቸው በተለየ መዝገብ በመመዝገባቸው ከሌላው በተለየ ማሸማቀቅ እየተፈጸመባቸው ነው፡፡
ይህን በተመለከተ ለማረሚያ ቤቱ አቤት ቢሉም ሊሻሻል አለመቻሉን ተከሳሾቹ ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤቱ ለማረሚያ ቤቱ አስተዳደር ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም አቤቱታቸውን ተቀብሎ በቀጣይ ቀጠሮ የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር ስለጉዳዩ ቀርቦ እንዲያስረዳ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

No comments:

Post a Comment