Wednesday 25 February 2015

ምሕረት ኢተፋ:- የኦሮሞ ህዝብ የነፃነት ጥያቄና አምባገነናዊ ጭቆና

በምሕረት ኢተፋ*
የመላው የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ የነጻነት ጥያቄ ነው:: ነጻ አእምሮ የሌለው፣ ነጻ አስተሳሰብ የለውም:: ኢትዮጵያ ውስጥ የኦሮሞ ህዝብ መብት ተከብሮ አያውቅም:: የወያኔ መንግስት ፀረ-ህዝብ፣ ፀረ ዲሞክራሲ፣ ፀረ ኦሮሞ ነው ብዬ ብገልጽ፣ የአደባባይ ሃቅ ነው። አምባገነን ገዢዎች ኦሮሞን በነጻነቱ እንዲኖር ከመፍቀድ ይልቅ፣ ለፖለቲካቸው መጠቀሚያ በማድረግ ጭቆናና ግፍ፣ እስራትና ሞት ከእለት ወደ እለት እያደረሱበት ይገኛሉ::
የኦሮሞ ህዝብ ሰለ ነጻነቱ መታገል ከጀመረ ብዙ አመታት ሆኖታል:: ዛሬም በትግል ላይ ነው:: የምንፈልገው ነጻነት እስኪመጣ ድረስ እንታገላለን:: የኦሮሞ ህዝብ ሰራተኛ፣ የተማረ፣ ሰው አክባሪ፣ አገሩን ለማሳደግ የሚደክም ህዝብ ነው:: የአሁኑ የወያኔ የዉስጥ-ገዳይ የአገዛዝ ስልት ደግሞ፣ የሰሚ ያለህ ብሎ የሚያስጮህ፣ የሚያስመርር ጉዳይ ነው።
በአሁኑ ወቅትም በሃገር ዉስጥ በኦሮሞ ወጣቶች የሚደረግ የነፃነት ትግል እየጠነከረ በሚሄድበት ግዜ ሁሉ ወያኔ መነሻው “የኦሮሞ ነፃነት ግንባር” (ኦነግ)
ነው በሚል በተለመደው የሂሳብ ስሌቱ የኦሮሞ ልጆችን እየገደለና እያፈሰ እስር ቤት ከማጎር አልፎ የኦሮሞን ህዝብ የነፃነት ጉዞ ለማዳከም የተለያዩ መርዛማ ዘዴዎችን በመጠቀም የኦሮሞ ህዝብንና የነፃነት ትግልን ለመለያየት ብሎ ለሰው ልጆች የማይገባን የጭካኔ ግፍ እየተገበረ ይገኛል።
ኦነግ በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ድርጅት ብቻ ሳይሆን የኦሮሞ ህዝብ የማንነትም መገለጫ ነው:: በበአለም የፀረ-አሸባሪነት ህግ የወጣው በዋናነት ንፁሃን ህዝቦችን ከሽብር ለመከላከል ሲሆን፣ የፀረ-አሸባሪነት ህግ በወያኔ በኢትዮጵያ የወጣበት ዋናው ምክንያት ግን ንፁሀን የሆኑትን የኦሮሞ ልጆችንና ሌሎችንም ለማሸበር ታስቦ የወጣ መሆኑ ግልፅ ነው። በሌላ አነጋገር አለም የፀረ-አሸባሪነትን ህግ የምትጠቀመው ንፁሃን ህዝቦች እንዳይሸበሩ ለመከላከል ሲሆን ወያኔ ግን ንጹሃን ህዝቦችን እራሱ እያሸበረበት ይገኛል።
One1Oromo2015
በሀገር ውስጥ ከሚያደርሱት በደል በተጨማሪ የእነሱን የግፍ አገዛዝ በመሸሽ ወደ ጎረቤት ሀገራት ሄደው በፖለቲካ ጥገኝነት ተመዝግበው የሚኖሩትን የኦሮሞ ልጆች እንኳ በሰላም እንዳይኖሩ ባሉበት በማሳደድ የፀረ-አሸባሪነት ህግን በሽፋን በመጠቀም ከጎረቤት መንግስታት ጋር ስምምነት ፈጥረው እጅ እግር አስረው በመመለስ የእድሜ ልክና የሞት ቅጣት ቀማሽ እንዲሆኑ እየተደረገ መሆኑ የዚህን ህግ አስከፊነትን ያመለክታል። እንደ ምሳሌነት ብናነሳ ተስፋሁን ጨመዳ እና መስፍን አበበ ከኬንያ የተያዙበት ዘዴና በወያኔ እስር ቤት ውስጥ የደረሰባቸው አሰቃቂ ግድያ መላውን የኦሮሞ ህዝብ ያስለቀሰ፣ ለበለጠ ትግል ያነሳሳ ጉዳይ ነው። በአሁኑ ግዜም በዚህ የወያኔ ፀረ-ሽብር ህግ ምክንያት በጎረቤት ሀገራት በፖለቲካ ጥገኝነት የሚኖሩ የኦሮሞ ልጆች ተሰሚነት እያጡ በስጋት ውስጥ እየኖሩ መሆኑን በተደጋጋሚ እየሰማን ነው።
ስለዚህ የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ እስኪመለስና ኦሮሞ በራሱ ሀገር ላይ የባለቤትነት መበቱን እስኪጎናፀፍ ድረስ ወያኔ ለግዜው እንዲሁ ይለፋል እንጂ የኦሮሞን የነፃነት ትግል ለማዳከምም ሆነ ለማጥፋት መላውን የኦሮሞን ህዝብ ካልጨረሰ በቀር መቼም እንደማይሳካለት ለማሳሰብ እወዳለሁ። አንድ ቀን እሮሞ ነፃ መውጣቱ ስለማይቀር ነፃነቱን ያገኘ ቀን ግን ግፈኞች ላደረሱት በደል ወንጀለኞቹን ከጥቅም አጨብጫቢዎቻቸው ጭምር በፍርድ እንደሚፋረዳቸው አንዳች ጥርጥር የለዉም::
ድል የኦሮሞ ህዝብ!

No comments:

Post a Comment