Saturday 20 September 2014

ሁለት ላሞች/የስርዓተ ማህበሮች ትርጓሜ,


two-cows
የየዘመኑን ስርዓተ ማህበር ምንነት ቅልጥጥ አድርጎ ለማሳየትና የማያሻማ ፍቺ ለመስጠት የየሀገሩ የቱርጁማን ጠበብት ያልቧጠጡት የሃሳብ ኮረኮንችና ያልዳሰሱት ሸካራ ብሂል የለም፡፡ በየዘመኑ ለተከሰቱ የማህበረሰብ አስተሳሰቦች ከተለያዩ ምሁራን የተለያየ ፍቺና ትርጓሜ ተሰጥቷል፡፡ ምሁራኑ በዘመናችን ከደረሱበት መተርጉም አንዱ በሁለት ላሞች ተምሳሌትነት የቀረበው ነው፡፡ የነጠረውን ፍጹማዊ መተርጉም እስኪያገኙ ድረስ የፈረንጅ ሊቃውንት ይህንን በሁለት ላሞች ላይ የተመሰረተ ተምሳሌታዊ መተርጉም ሰጥተዋልና ከግልዎ ግምገማ ጋር በማያያዝ ይህችን አጭር ሐተታ ያነጻጽሩት ዘንድ እነሆ ብለናል፡፡
1. ሶሻሊዝም
እርስዎ ሁለት ላሞች ይኖርዎታል እንበል፡፡ በሶሻሊዝም ስርዓተ-ህይወት እስካሉ ድረስ አንዲቷን ላም ለራስዎ መድበው ሌላይቱን ለጎረቤትዎ መዳረግ ግዴታዎ ነው፡፡
2. ኮሚኒዝም
እርስዎ ሁለት ላሞች ይኖርዎታል እንበል፡፡ በኮሚኒዝም ስርዓተ ማህበር ውስጥ እስካሉ ድረስ መንግሥታዊው የኮሚኒስት ፓርቲ ሁለቱንም ላሞችዎን ይወስድብዎትና የድርሻዎ ያህል ብቻ ወተት ያድልዎታል፡፡
3. ፋሺዝም
እርስዎ መንታ ላሞች አሉዎት እንበል፡፡ በፋሺዝም ስርዓ-ህይወት እስካሉ ድረስ የሚገዛዎ የመንግሥት ቁንጮ ሁለቱንም ላሞችዎን ይነጥቅና የሚያልበውን ወተት ለራስዎ ይሸጥልዎታል፡፡
4. ናዚዝም
እርስዎ መንታ ላሞች አሉዎት እንበል፡፡ በናዚዝም ስርዓተ-ሕይወት እስካሉ ድረስ ጨካኙ መንግስት ሁለቱንም ላሞችዎን ዘርፎ ከወሰዳቸው በኋላ ራስዎን ጭምር ያርድዎታል፡፡
5. ቢሮክራሲዝም
እርስዎ ጥንድ ላሞች አሉዎት እንበል፡፡ የሚኖሩበት ስርዓተ ማህበር ቢሮክራሲዝም እስከሆነ ድረስ ሁለቱንም ላሞች ይወስድብዎትና አንደኛይቱን ያርዳታል፤ ሌላይቱን ግን እያለበ ወተቷን እመቅ ያፈሰዋል፡፡
6. ካፒታሊዝም
እርስዎ የሁለት ላሞች ባለቤት ነዎት እንበል፡፡ የሚኖሩበት ስርዓተ ማህበር ካፒታሊዝም እስከሆነ ድረስ በዘዴ ይወስድብዎና አንዲቷን ላም ከሸጠ በኋላ ለገዛ ራሱ ለማራባት ሲል በተሸጠችው ላም ገንዘብ ኮርማ ይገዘባበታል፡፡
ማን ቀረ? ማኦይዝም፤… ሌኒንዘም፣ . .. ራዲካሊዝም፣… ሊብራሊዝምኒኦ-ሊብራሊዝምአብዮታዊ ዲሞክራሲ ወዘተ… አሉ፡፡ እስቲ በዚህ የሁለት ላሞች ቀመር መሰረት ራስዎ የሚኖሩበትን ስርዓተ ማህበር ለመተርጎም ይሞክሩ፡፡
*****
(ሀይሉ ገብረዮሐንስ፣ ኢትኦጵ መጽሔት፣ ቅጽ 3፣ ቁጥር 031፣ ታህሳስ 1994፣ ገጽ 4)
*****
በጉዳዩ ላይ ድረገጾችን ስንመለከት ያገኘነውን አንድ እኛ እንጨምር:-
7. የቻይና ዓይነት ኮሙኒዝም
እርስዎ መንታ ላሞች አሉዎት እንበል፡፡ እነዚህ ሁለት ላሞች በ300 ሰዎች ይታለባሉ:: ስርዓተ ማህበሩ ባገር ሁሉ ሥራዓጥነት በጭራሽ የለም፣ ምርታማነት አድጓል፣ ተመንድጓል፣ ህዳሴ፣ ውዳሴ ነው ይላል:: እውነት የሚዘግበውን ጋዜጠኛ ይረሸናል፡፡
—–
ጽሁፉን ያገኘነው ከAfendi Muteki ፌስቡክ ገጽ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment