Sunday 24 August 2014

የውሸት አባት 2ኛ ሙት ዓመት ነዶ የማያልቀው [ሻማ] የኢትዮጵያ ሕዝብ.

ግንቦት 20፣ 1983ዓም መለስ ወይም ለገሠ ወይም አስረስ ወይም ዜናዊ ወይም … ትክክለኛ ስሙን በውል የማናውቀው ከነጭፍሮቹ ቤተመንግሥት ገብቶ ራሱን አጼያዊ ፕሬዚዳንት፣ ቀጥሎም አጼያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ … በማድረግ ከሾመበት ቀን ጀምሮ የኢትዮጵያ ሕዝብ በኦፊሴል እንደ ሻማ ወይም እንደ ኩራዝ ተለኩሷል።
unnamedአቀጣጣዮቹ ምስለኔዎች ከሻማና ከኩራዝ ከፍ ብለው ብርጭቆ የለበሱ ፋኖሶች ሆነዋል። ለመለስና ለጭፍሮቹ የሚያበሩ ፋኖሶቹም (ኦህዴድ፣ ብአዴን፣ …)፣ ኩራዞቹም፣ ሻማዎቹም የበራላቸው ማሾዎች (ህወሃቶች) ሁሉም በአንድነት ዛሬ ላይ ደርሰዋል። ለኳሹም ተለኳሹም እያበሩ የአስለኳሹን ሁለተኛ ሙት ዓመት “እያከበሩ” ነው። በሌላ አነጋገር ለሙት መንፈስ እሣት አንድደው እየሰገዱ ነው። ተገድዶ እየነደደ ያለውን ሕዝብ፣ አዳዲሶቹ አስለኳሾች (የኃይለማርያም ደቦ አስተዳደር) ሕዝብን ሻማ ላደረገውና ከስሙ ጀምሮ በውል ማንነቱ ላልታወቀው ግለሰብ “ሻማ አብሩ” አሉለት።
  • ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ ለሁለተኛው ሙት ዓመት “የውርስ መታሰቢያነት” ከዚህ በታች ያለውን የመክብብ ማሞን ጽሑፍ ሲያቀርብ በመለስ ሞት ላዘኑ ሁሉ ለሃዘናቸው መጉመጥመጫ እንዲሆን በማሰብ ነው። “የውሸት አባት” መለስ ነፍስ ካወቀበት ጊዜ ጀምሮ ስዩመ አብዮታዊ ዴሞክራሲ አጼ አድርጎ ራሱን በመሰየም ሕዝብን እንደሻማ ባነደደበት ዘመናት ከአንደበቱ ሲወጡ የተመዘገቡ ውሸቶች ስፍር ቁጥር የላቸውም።
በተለይ ግን በ1997ቱ ምርጫ ሰሞን ሕዝብ እንደ ሻማ ከመቃጠልና ከመንደድ የራሱን መሪ እንዳይመርጥ የዋሸው ውሸት ከዚህ በታች ሰፍሯል። ታዲያ ሕዝብ እንደ ሻማ ከመቅለጥ የሚያድነውን እንዳይመርጥ ለገደበ ግለሰብ እንዴት ሻማ ይበራለታል?!
“ማሾዎቹ” ደረት ቢደቁ፣ ከበሮ ቢደልቁ፣ ፈንዲሻ ቢበትኑ፣ አሸንዳ ቢዘሉ፣ ሠርግና ምላሽ ቢያደርጉ፣ “አንጓይ ፍስስ” ቢሉ፣ … ምክንያት አላቸው። እንደ ዱር አውሬ “የአገር ቅርስ” ሲሉት ውለው ቢያድሩ ከልካይ ሊኖራቸው አይችልም። በሚሊዮን ሕዝብ ችግር ላይ ቆመው ለሙት መንፈስ ቢንደባለሉ ደንታ የላቸውም። ሚሊዮኖች በሚያዝኑበት አገር፣ እስር ቤትና ማጎሪያዎች ውሥጥ የታፈኑት ሲቃ በሚያሰሙበት አገር እነርሱ ሙት ዓመትን አስረሽ ምቺው ቢያደርጉት ማን ተዉ ሊላቸው ይችላል?! ምክንያቱም ብርሃን ይፈልጋሉ፤ ለዚያ ደግሞ ነዶ የማያልቅ ሻማ ያስፈልጋል።
ለማንኛውም መጪው የምርጫ ጊዜ ነውና የወደፊቱን ውሸት ከዚህ በታች በሰፈረው የመክብብ ማሞ ጦማር እያጣቀሳችሁ የ… ዜናዊን ሙት ዓመት አክብሩ። ለኢትዮጵያ እውነተኛ ስም ያለውና ለዘመናት በዚያው ስሙ የሚጠራ መሪ ይስጣት።
“ውሸታም!”
ሰሞኑን (ይህ ጽሁፍ የተጻፈው በመስከረም 2002/Sept. 2009 ነው) የመገናኛ ብዙሃንን ትኩረት የሳበ አንድ ክስተት በአሜሪካ ተፈጽሟል። ፕሬዚዳንት ኦባማ በምርጫ ዘመቻቸው ጊዜ ቃል የገቡለትን የጤና ጥበቃ ማሻሻያ አዋጅ እንዲጸድቅ የሕዝብ ተወካዮችን ሰብስበው ንግግር በሚያደርጉበት ወቅት ከተቃዋሚ የሪፓብሊካኑ ወገን የማርጎምገምና የተቃውሞ ድምጽ ተሰማ። በተለይ ግን የጤናው ማሻሻያ አዋጅ “ሕገወጥ ስደተኞችን አያካትትም” የሚል ንግግር ባደረጉ ጊዜ ከደቡብ ካሮላይናው እንደራሴ “ውሸታም!” የሚል ድምጽ አስተጋባ።
እንደ እውነቱ ከሆነ በረቂቅ ሕጉ ላይ ሕገወጥ ስደተኞች የጤና መድኅን ዋስትና እንደማያገኙ በማያሻማ መልኩ የሰፈረ ጉዳይ ነው። እዚህ ላይ “ማነው ውሸታም?” የሚለውን ለመመርመር አይደለም ጉዳዩን የጽሁፌ መነሻ ያደረኩት። ሆኖም ግን ይህንን የሰማሁ ምሽት እንደራሴው ኢትዮጵያ ቢሆኑ ኖሮ ከምርጫ 97 ጀምሮ እስካሁን (2002ዓም) ድረስ ምን ያህል ጊዜ “ውሸታም!” እያሉ ይጮኹ ይሆን በማለት ያለፉትን አምስት ዓመታት (1997-2002ዓም) በምናቤ መቃኘት ጀመርኩና ከዚህ በፊት የተደረጉ ቃለመጠይቆችን ለመመርመር ወደኋላ ሄደኩ።
ማርክሲስታዊው ህወሃት ከበረሃ ወጥቶ የምኒልክን ቤተመንግሥት ከተቆጣጠረበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት 18 (አሁን 23) ዓመታት ከአመራሮቹ ስንሰማ የቆየነው ውሸት ጆሮ የሚገነጥል ሲሆን በተለይም የኢትዮጵያ ሕዝብ ድምጽ ከተሰረቀበት 1997ዓም ጀምሮ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ” ለተለያዩ ምዕራባዊ የመገናኛ ብዙሓን “ሥልጣኔን እለቃለሁ” በማለት ሲቀደድ የነበረው ከቁጥር በላይ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ጥቂቱን ግን ከዚህ በታች አቅርቤዋለሁ። (ከአዘጋጆቹ፤ መለሳውያን በሙሉ የሙቱን መንፈስ 2ኛ ዓመት ስትዘክሩ የውሸት ውርሱንም አትዘንጉ)።
የቢቢሲው ጋዜጠኛ ስቲፈን ሳኩር ከምርጫ 97 በኋላ ለ“ጠቅላይ ሚኒስትር” ዜናዊ ሰኔ 27 ቀን 1997 ዓም ቃለመጠይቅ ባደረገበት ወቅት የሚከተሉትን ጥያቄዎች ጠይቆት ነበር።candle1
ስቲፈን፡- አሁን ስላለው አጀንዳ እንድጠይቅ ይፈቀድልኝ። እንደው እንደበልና የምርጫው ውጤት ፓርቲህን አሸናፊ አደረገው እንበል እና ይህ ከሆነ እንደገና ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት እንደገና በሥልጣን ላይ ትቆያለህ?ዜናዊ፡- ያ ፓርቲዬ የሚወስነው ጉዳይ ነው።
ስቲፈን፡- አንተ ግን ምን ለማድረግ ነው የምትፈልገው?ዜናዊ፡- እኔ ማድረግ የምፈልገውን ቆየት ብዬ የማስብበት ነው። ውሳኔዬም በሁኔታዎች ላይ የተመሠረተ ነው።
ስቲፈን፡- በእርግጥ ማድረግ የምትፈልገውን ወስነሃል። ማለቴ ለመመረጥ ተወዳድረሃል፤ ይህም ማለት ሥልጣኑን ትፈልገዋለህ ማለት ነው። (በሥልጣን መቆየት ባትፈልግ አትወዳደርም ነበር)ዜናዊ፡- ሥልጣኑን የምፈልገው አገሬን ለማገልገል ነው። የማገለግለው ግን የምጨምረው እሴት ሲኖር ነው። … የምጨምረው እሴት አለኝ። ይህንንም እቀጥልበታለሁ የምጨምረው እሴት እስካለኝ ድረስ። በተመሳሳይ መልኩ ፓርቲዬ እሴት የማልጨምር መስሎ ሲያገኘው በማንኛውም ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊቀይር ይችላል።
“ውሸታም!”
ህወሃት/ኢህአዴግ ምርጫውን ካጭበረበረ 1 ዓመት ከ7 ወር በኋላ የዋሽንግተን ፖስት ጋዜጠኛ ስቴፋኒ ማክሩመን ታህሳስ 5፤1999ዓም ተመሳሳይ ጥያቄ አቅርባ ነበር።
ስቴፋኒ፡- ለሦስተኛ ጊዜ ለመመረጥ ዕቅድ አለህ?ዜናዊ፡- ፓርቲዬ? ፓርቲዬ ለሦስተኛ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ለአስረኛ ጊዜም ቢሆን ሊሞክር ይችላል።
ስቴፋኒ፡- አንተስ በግልህ?ዜናዊ፡- እኔ በግሌ ይበቃኛል ነው የምለው።
“ውሸታም!”
ቀጥሎም ከዘጠኝ ወር በኋላ አሌክስ ፔሪ ከ“ታይም” መጽሔት ጳጉሜ 1፤1999ዓም የሚከተሉትን ጥያቄዎች አቀረበ።
አሌክስ፡- አብዛኛውን ጊዜ የአፍሪካ መሪዎች ሥልጣን ለመልቀቅ ሲያመነቱ ይስተዋላሉ። ሆኖም ግን ከዚህ በፊት በሥልጣን እንደማትቆይ ፍንጭ ስትሰጥ ቆይተሃል።ዜናዊ፡- አሁን ሦስት ዓመት ብቻ ነው የቀረኝ።
አሌክስ፡- ከዚያ ሥልጣንህን ትለቅቃለህ?ዜናዊ፡- ከዚያማ ሒደቱ ይቀጥላል።
አሌክስ፡- ለምንድነው ሥልጣን መልቀቅ የምትፈልገው?ዜናዊ፡- እስካሁን ብዙ ቆይቻለሁ። ከዚህ በኋላ ባለው ጊዜ አዲስ ነገር ለማድረግ የማስብበት ይሆናል።
“ውሸታም!”
ዜናዊ ቀጣዩን ቃለመጠይቅ ሲያደርግ ደግሞ ከታይም መጽሔቱ አሌክስ ጋር ያደረገው ሦስት ወር እንኳን አልሞላውም ነበር። ጠያቂው የአልጃዚራው መሃመድ አዶው ምልልሱን ያደረገው ኅዳር 12፤ 2000ዓም ነበር።
መሃመድ፡- በቅርቡ ከጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥልጣን የመልቀቁን ጉዳይ እያሰብክበት ነውን?ዜናዊ፡- ከዚህ በፊት እንደተናገርኩት በጠቅላይ ሚኒስትርነት የማገለግልበት ይህ የመጨረሻው የሥልጣን ዘመኔ ነው (2002ዓም ማለቱ ነበር)።
“ውሸታም”
በዚሁ በ2000ዓም ግንቦት 4ቀን awate.com ከተሰኘ ድረገጽ ጋር ቃለምልልስ ያደረገ ሲሆን ጠያቂውም ሳሌህ ጆሃር ነበር።
ሳሌህ፡- በህይወት ዘመኔ ከሥልጣንህ ለቅቀህ “የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር” እየተባልክ በመጠራት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በማስተማር፣ መጽሐፍ በመጻፍ ወይም አንድ ፋውንዴሽን ስትመራ የማይበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? እስቲ ንገረኝ።ዜናዊ፡- በጣም ትክክል ነው። እኔም ያንን ቀን እየናፈኩት ነው። ሩቅ እንደማይሆን አስባለሁ።
ሳሌህ፡- ይህ ማለት እንግዲህ ለሌሎች ሁሉ ምሳሌ ትሆናለህ ማለት ነው?ዜናዊ፡- ምንም ጥርጥር የለውም። ነገን ልትኖረው እንደምትችል እርግጠኛ ልትሆን አትችልም። ሆኖም ግን እንደማንኛውም ሰው እኖራለሁ ብዬ በማሰብ ከሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት በኋላ (ከ2002ዓም ጀምሮ ማለቱ ነበር) “የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር” ብለህ ልትጠራኝ ትችላለህ።
“ውሸታም!”
ውሸቱ ግን በዚህ አላቆመም። በመጋቢት 24፤ 2001ዓም የቢቢሲዋ ዘይነብ ባዳዊ ቃለመጠይቅ ባደረገችለት ጊዜ ይህንኑ ሥልጣን የመልቀቅ ጥያቄ አንስታ ነበር።candle 2
ዘይነብ፡- ከዚህ በፊት (ባቀረበችው ጥያቄዎች) እንደጠቆምኩት ከ1983 ዓም ጀምሮ በሥልጣን ላይ ነበርክ። አንዳንድ ጊዜ ከሥልጣን የምትለቅበት ጊዜ እንደደረሰ ስትናገር ቆይተሃል። ሌላ ጊዜ ደግሞ ራስህን የፓርቲህ ወታደር አድርገህ ስትናገር ትደመጣለህ። መቼ ነው (ከሥልጣን የምትለቅበትን) እርግጠኛውን ቀን የምትነግረን? ምክንያቱም ከምናያቸው ነገሮች ስንነሳ ይህ በአፍሪካ መሪዎች ዘንድ የሚታየውን “ያለኔ …” የሚለውን አስተሳሰብ ትደግፋለህ እንድንል እያደረከን ነው ያለኸው። ማለትም ምትክ የሌለው መሪ ዓይነት (እየሆንክ ነው)፤ ለሁለት ዓስርተ ዓመታት በሥልጣን ቆይቻለሁ የሚል ዓይነት?ዜናዊ፡- ራሴን ምትክ የሌለው መሪ አድርጌ አላውቅም። እናም ማንኛውም ሰው ራሱን ለፓርቲም ሆነ ለአገር ምትክ የሌለው አድርጎ የሚቆጥር ከሆነ ያ ፓርቲም ሆነ አገር መኖር ይገባዋል ብዬ አላምንም።
ዘይነብ፡- ታዲያ መቼ ነው ቁርጥ ያለውን ቀን የምትናገረው?ዜናዊ፡- ፓርቲዬ ካቀረብኩት ዕቅድ ጋር ሲስማማ ያኔ ይሆናል።
ዘይነብ፡- ዕቅድህ ምን እንደሆነ ልትነግረን ትችላለህ? በ2002ዓም ምርጫ ይካሄዳል?!ዜናዊ፡- ዕቅዴማ ይህ የመጨረሻው የሥልጣን ዘመኔ እንደሚሆን ማረጋገጥ ነው።
“ውሸታም!”
በዚህ አላበቃም! ሰኔ 10፤2001ዓም የፋይናንሺያል ታይምስ የአፍሪካ ቢሮ አርታኢ የሆነው ዊሊያም ዋሊስ ይህንኑ ማለቂያ የሌለውን የሥልጣን መልቀቅ ጥያቄ አቅርቦ ነበር። ሆኖም አጠያየቁን ቀየር አድርጎት ስለነበረ የውሸቱ ለከት የት እንደደረሰ በግልጽ እንዲያሳይ አድርጎታል።
ዊሊያም፡- ከዚህ ቀደም ከሥልጣን ለመውረድ ፈቃደኛ እንደሆንክ ስትናገር ቆይተሃል። በዚህ ዙሪያ ያለውን እንቅስቃሴ ምን እንደሚመስል ብታስረዳን?ዜናዊ፡- በአሁኑ ጊዜ በፓርቲያችን ውስጥ ውይይት እያደረግን ነው። ይህም በፓርቲያችን ውስጥ የምናደርገው ውይይት ሰዎች ሊገምቱት ከሚችሉት በላይ በጣም ብስለት የተሞላበት ነው። ስለ መለስ ብቻ አይደለም የምንነጋገረው። በትጥቅ ትግሉ የተሳተፈው የቀድሞው ትውልድ በአዲስና የትጥቅ ትግል ተሞክሮ በሌለው ትውልድ እንዴት ሊተካ ስለሚችልበት ሁኔታ እየተወያየን ነው። ለፓርቲያችን ሲባል ይህ መሆን ያለበት ጉዳይ ነው። ስልትን በተመለከተ ማለትም ጊዜው መቼ ይሆናል የሚለው ቁርጥ ያለ መልስ ላይኖር ይችላል። (ምርጫ መጣ ክህደት ተጀመረ) ክርክሩም በዚሁ የሚቀጥል ነው። ሆኖም ግን የቀድሞው አመራር በአዲስ መተካት አለበት በሚለው ላይ ግን አለመስማማት የሚባል ነገር አይኖርም። ይህ ከመፍትሔዎቹ አንዱ ነው፤ ብቸኛው መፍትሔ ግን አይደለም። ስለዚህም የእኛ ግምባር በአመዛኙ ሌሎች ግምባሮች ከሚያጋጥማቸው የመፈረካከስ አደጋ አምልጧል ብዬ አምናለሁ።
ዊሊያም፡- እና የሚቀጥለው ዓመት (2002 ማለቱ ነበር) በሚደረገው ምርጫ አትወዳደርም ማለት ነው?ዜናዊ፡- እያልኩ ያለሁት እኔ በግሌ ይበቃኛል ነው የምለው። እኔ ብቸኛው ተኳሽ አይደለሁም። ለበርካታ ጊዜያት ጠቅላይ ሚኒስትር በነበርኩበት ጊዜም በድምጽ ብልጫ በመሸነፍ የማልፈልገውን ነገር ሳደርግ ቆይቻለሁ። በተለይም በኤርትራ ጦርነት ወቅት ሳልፈልገው የማልስማማበትን ሆኖም ግን የፓርቲዬ ውሳኔ በመሆኑ ብቻ ያንን ሳስፈጽም ኖሬአለሁ። በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ወቅት ሁለት አማራጮች አሉኝ። ለሥልጣን መልቀቅ ወይም የብዙሃኑን ውሳኔ መቀበል። ይህ ሲሆን እኔ የራሴን አቋም አቀርባለሁ፤ ሌሎችም የራሳቸውን አቋም ያቀርባሉ፤ ክርክሩም ይቀጥላል። ተስፋ የማደርገው ሁላችንም አንድ የመግባቢያ ነጥብ ላይ እንደርሳለን ብዬ ነው። ያም ሲሆን እኔም ህይወቴን ሙሉ ከተዋጋሁለት ፓርቲዬ መልቀቅ ሳያስፈልገኝ እንደቀጥል ይሆናል። ከመንግሥት ሥልጣኔ ከለቀቅሁ በኋላም እንኳን በፓርቲዬ በአባልነት መቀጠል እፈልጋለሁ። እናም ተስፋ የማደርገው ሁላችንም አንድ የመግባቢያ ነጥብ ላይ እንደርሳለን ብዬ ነው። ልዩነቶቻችን ደግሞ ያንን ያህል ትልቅ አይደሉም።
ዊሊያም፡- ታዲያ ይህ የሚሆነው መቼ ነው? በቅርቡ የምታደርጉት የፓርቲ ስብሰባ አላችሁ?ዜናዊ፡- አዎን፤ መስከረም ላይ ስብሰባ አለን።
ዊሊያም፡- እናም ያኔ ነው በውሳኔው ላይ የምትከራከሩት?ዜናዊ፡- አዎን፤ ግን ከዚያ በፊት ውይይቱ ይካሄዳል፤ …
ዊሊያም፡- ወደፊት ማነው የሚተካህ?ዜናዊ፡- ያንን ውሳኔ ለፓርቲዬ እተወዋለሁ፤ …
ዊሊያም፡- ኢትዮጵያውያን ለምንድነው በእርግጥ ሥልጣን ትለቃለህ ብለው የማያምኑት?ዜናዊ፡- ምክንያቱም ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ ሲደረግ ስላላዩ ነው።
ዊሊያም፡- ነገር ግን እያደረክ ያለው ያንኑ የሚከተል እንደሆነ ነው።ዜናዊ፡- እኔ ይህንን ዓይነት አስተሳሰብ ለማስወገድ ነው የምፈልገው፤ …
ዊሊያም፡- እናም ይህ ማለት ሙሉ በሙሉ ከማንኛውም ተግባር ትገለላለህ ማለት ነው?ዜናዊ፡- ያ ካልሆነማ የአመራር ለውጥ ሊኖር አይችልም። ነገር ግን ያንን ካደረግን በኋላ ፓርቲዬ ወይ መጽሐፍ እያነበብኩና እየጻፍኩ እንድቀመጥ ወይም ሌላ የፓርቲ ሥራ እየሠራሁ እንድቀጥል ይወስናል።
ዊሊያም፡- የፓርቲ ሥራ ማለት ሊቀመንበርነት?ዜናዊ፡- አይመስለኝም፤ ምክንያቱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርቲው ሊቀመንበር መሆን አለበት። ያ ደግሞ ጡረታ ለወጣ ሰው ሊሰጠው የሚገባ ሥልጣን አይደለም።
“ውሸታም!”
እንግዲህ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደዚህ ዓይነት ቅጥፈት (እና ተራ የቁጭ በሉዎች ቀደዳ) ላለፉት 18ዓመታት (ጽሁፉ በ2002ዓም የተጻፈ ነው) ሲቀደድለት ቆይቶ ህወሃት በሚቆጣጠረው ቴሌቪዥን ለአዲሱ ዓመት አዲስ ዜና – ትኩስ ዜና – ሰበር ዜና – ተሰበረለት። “ምትክ አልባው ጠቅላይ ሚኒስትር ከመጪው 2002 ጀምሮ ሥልጣናቸውን ለአምስት ዓመታት እንዳራዘሙት …” አበሰረልን። ሞት ቀድሞ candle bombበ“ውርስ” መታወቅ ጀመረ እንጂ በመጪው 2007 ምርጫም ወይ ፍንክች ይል ነበር። መለስ “ሥልጣኔን እለቃለሁ” ሲል ፓርቲው ደግሞ “አትለቅም” እያለ ገመድ ሲጓተቱ ኖረው የመለስ ሞት ለምን የሰማዕት ሆነ? “አልለቅም” ያለው የፓርቲው (ኢህአዴግ) ስህተት መሆኑ በግልጽ እየታወቀ እስካሁን ድረስ በተለይ የህወሃት ፖሊት ቢሮ አባላት መሪያቸውን “አንድደው በመግደል” ለምንድነው ያልተከሰሱት?
ውሸታሙን መለስ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከተገላገለው ሁለት ዓመት ሆኗል። የውሸቱ መጠን ቀንሷል ለማለት ባይቻልም ሕዝብ ግን በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉትን የተቀናቃኝ ፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆነ ህወሃት/ኢህአዴግ የሚያቅሙትን ውሸት እየሰማ ይታዘባል፤ ታሪክም ትዝብቱን ይመዘግባል።
ታዲያ ላለፉት 23ዓመታት “የኤሌክትሪክ ኃይል” በነጻነት በሌላት አገር ራሱን ሻማ አድርጎ ሲያበራ በግፍ የኖረ ሕዝብ ለምን በግድ “ሻማ አብራ” ማለት ያስፈልገዋል? ግፍን የሚያይ አለ! ያንን ግፍ ቆጥሮ ደግሞ ፍዳ የሚያስቆጥር፤ በሰፈሩት መስፈሪያ የሚሰፍር ከሁሉ የበላይ፤ ልዕለኃያል አለ። ነዶ የማያልቀው ሕዝብ እየደረሰበት ያለውን ግፍ ይመለከታል። “አንድ ቀን ግፍ ወደተነሣበት ይመለሳል”።

No comments:

Post a Comment