Monday 7 April 2014

ማዕከላዊ እስርቤት ከፍተኛ ስቃይ ይደርስባቸዋል በሚል ተሰግቷል.

የኢህአዴግን ካዝና የምትሞላዋ ኖርዌይ በማዕከላዊ እስር ቤት የሚገኙትን ዜጋዋን አስመልክቶ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እየሰራች መሆንዋ ታወቀ። በማዕከላዊ እስር ቤት የታሰሩት ዜጋዋ ድብደባና ቶርቸር እንዳይካሄድባቸው በቅርብ ክትትል እያደረገች መሆንዋን ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ክፍሎች ለጎልጉል አስታውቀዋል።

ኢህአዴግን ከልጅነቱ ጀምራ ስትደጉም የኖረቸውና አሁን ደግሞ “በልማታዊ መንግሥትነት” መድባ ድጋፏን የምትዘረጋለት ኖርዌይ ዜጋዋን አስመልክቶ አስፈላጊውን ሁሉ የማድረግ ግዴታ እንዳለባት ይታወቃል። በዚሁ መሰረት የኖርዌይ ትልቁ ጋዜጣ ቀደም ሲል ጎልጉል ምንጮቹን ጠቅሶ ይፋ ያደረገውን ዜና የሚያረጋግጥ ዜና አሰራጭቷል።

ደቡብ ሱዳን የጸጥታ ሃይሎች አሳልፈው ለኢህአዴግ የሰጧቸው የቀድሞ የጋምቤላ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦኬሎ አኳይ የኖርዌይ ዜግነት እንዳለቸው በማረጋገጥ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጉዳዩን በቅርበት እንደሚከታተለው፣ አዲስ አበባ የሚገኘው የኖርዌይ ኤምባሲም ስራውን እየሰራ እንደሆነ አፍተን ፖስት አመልክቷል።

አፍተን ፖስት “የሰብአዊ መብት ተከራካሪ” ሲል በዜናው መክፈቻ የጠቀሳቸውን አቶ ኦኬሎ አኳይን አስመልክቶ የውጪጉዳይ ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን አማካሪ ስቫይን ሚኬልሰንን ጠቅሶ “አቶ ኦኬሎ የደቡብ ሱዳን የደህንነት ሃይሎች በደቡብ ሱዳንና በዩጋንዳ ድንበር መካከል ይዘዋቸዋል። አንደተያዙም ወደ ጁባ ሳይወሰዱ ተላልፈው ተሰጥተዋል” በማለት የጉዳዩን አካሄድ አመላክቷል።

የኢህአዴግን የገቢ ምንጭ የሆነችው ኖርዌይ በጉዳዩ አቋም በመያዝ ያስታወቀችው ስለመኖሩ ዜናውን የዘገበው አፍተን ፖስት ያለው ነገር የለም። ይሁን አንጂ ድርጊቱን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ኖርዌይ እንደምትቃወመው አልሸሸገም። አቶ አኳይ ለምን ወደ ስፍራው እንደተጓዙ በውል የተገለጸ ነገር እንደሌለ ዜናው ጠቁሟል። “በተመሳሳይ” በማለት ከዜናው ግርጌ ኢህአዴግ ለዴሞክራሲና ለሰብአዊ መብት ክብር እንደሌለው፣ በነጻ ፕሬስና በተቃዋሚ ፓርቲዎች ላይ እያደር የከረረ ርምጃ በመውሰዱ ክፉኛ የሚዘለፍበት ጉዳይ እንደሆነ አጣቅሷል።

ጎልጉል መጋቢት 19 ቀን 2006 ዓም (March 28, 2014) ቀን ዜናውን ይፋ በማውጣት ቅድሚያ ወስዶ ሲዘገብ አቶ ኦኬሎ ከደቡብ ሱዳን ከሆቴል ውስጥ ታፍነው መወሰዳቸውን ጠቁመን ነበር። አሁን አዲስ በመጣው መረጃ በዩጋንዳና በደቡብ ሱዳን ድንበር ላይ ተያዙ መባሉ ምን አልባትም ኢህአዴግ ሊመሰርትባቸው ላሰበው ክስ አመቺ ሁኔታ ለመፍጠር ታስቦ እንደሚሆን ጥርጣሬ አለ። የዜናው ምንጭ አቶ ኦኬሎ ከጁባ በሄሊኮፕትር መወሰዳቸውን እንደሚያውቁ ገልጸዋል።

በመለስ ዜናዊ ውሳኔና ትዕዛዝ በአኙዋክ ተወላጆች ላይ በጅምላ የተከናወነውን ጭፍጨፋ አስመልከቶ ተቃውሞ በማሰማት፣ አድርጉ ተብለው የታዘዙትን ባለመቀበል አገር ጥለው የኮበለሉት አቶ ኦኬሎ ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ያገባናል በሚሉ “አክቲቪስቶች”፣ የፖለቲካ ድርጅቶችና፣ ማህበራት ዘንድ ዋንኛ ርዕስ ያለመሆናቸው ምክንያት አስገራሚ እንደሆነባቸው የሚጠቁሙ ዲያስፖራዎች ጥቂት አይደሉም። ከዚያም አልፎ አሁንም የመታሰራቸው እና እርሳቸውን ለማስፈታት በሚደረገው ሁኔታ ላይ የተፈጠረው ዝምታ አጠያያቂ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡

No comments:

Post a Comment