Wednesday, 19 November 2014

ዳንኤል ታደሰ:- ያጣነውን መብትና ነጻነታችንን በእጃችን ለማስገባት ዛሬውኑ እንነሳ

በዳንኤል ታደሰ*
ሃገራችንና ወገኖቻችን ለኢኮኖሚና ማሕበራዊ ችግሮች ከመጋለጥ አልፈው አደገኛ አጣብቂኝ ውስጥ ናቸው፡፡ ለሕዝቡና ለሀገሪቱ ጥቅም የሚቆም ብቃት ያለው አስተዳደር የለም፡፡ ህግ አለ፣ ህገ መንግስት አለ፣ ቢባልም ተገቢ ያልሆኑና ከሕገ-መንግሥቱ ጋር የሚቃረኑ አፋኝ፣ አስደንጋጭ እና ኢሰብአዊ ሕጐችና ደንቦች በተከታታይ ይወጣሉ፡፡ እነኚህም ሕዝቡን በተደራራቢነት እያስጨነቁት ይገኛሉ፡፡ ህጐችና ደንቦች ሲወጡ ሕዝብ መወያየትና መምከር ሲገባው፣ ውይይት ሳይደረግባቸው በዘፈቀደ እና ባልሰለጠኑ የመንግስት ካድሬዎች ተግባራዊ ሲሆኑ ይታያል፡፡
የወጡና የፀደቁ ሕጐች ላይም ሆነ በአፈፃፀም ላይ ችግሮች ሲፈጠሩ ማየት የሚኖርበት ፍርድ ቤት ነበር፤ ነገር ግን በሚወጡ ሕጐች የፍ/ቤት ሥልጣን ተነጥቆ ለኤጀንሲዎችና ለባለስልጣናት እንዲሁም ለሌሎች ባልበሰሉ ካድሬዎች ለተሞሉ መስሪያ ቤቶች እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡ ከዚህ አኳያ ስናይ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት ህዝባችን አግኝቷል ወይ? የሚል ጥያቄን አስነስቶ ከመሰላቸታችን የተነሳ በኢትዮጵያ ሕግና መንግስት እንደሌለ ለማንም ግልጽ ነው።
ባለፉት 23 ዓመታት የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አባላት ናችሁ በሚል እጅግ በጣም ብዙ ኦሮሞዎች ታስረዋል፣ ተሰደዋል ወይም ተገድለዋል። ይህ ሁኔታ አሁንም በሰፊው ቀጥሏል። የአሁኑን ለየት የሚያደርገው ክሱ “ራሱን ኦነግ ብሎ ከሚጠራው ‘አሸባሪ’ ድርጅት ውስጥ አባል በመሆን …” ወደሚል በመቀየሩ ለነጻነታችን የምናደርገውን ትግል ሲያጣጥለው ይታያል።
ቀደም ብሎ በመሰረቱት ክሶች ደልዴሳ ዋቆ ጃርሶ፥ ገልገሎ ጉዮ ቦሩ እና ዋርዮ ጣጤሳ ጉዮ የተባሉ ግለሰቦች የኦነግ አባል በመሆናቸው ‘የሽብርተኝነት ድርጊቶችን’ ሲፈፅሙ ይዣቸዋለሁ’ በማለት የፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉን በመጥቀስ ክስ መስርቷል። በተመሳሳይ ሁኔታ የፌደራል ዓቃቢ ሕግ ባቀረበው ‘የሽብር ወንጀል’ ክስ የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የነበሩት አብዲ ከማል የሱፍና ቶፊቅ ረሽድ ዩያ ‘የአሸባሪው’ ድርጅት የኦነግ አባላት በመሆን የሽብር ተግባራትን ልትፈፅሙ ስትሉ ተይዛችኋል’ ተብለው የፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉ አንቀፅ ተጠቅሶባቸው ክሳቸውን በማረፊያ ቤት ሆነው እየተከታተሉ ይገኛሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ባለፈው አመት በኦሮሚያ ክልል በነበረው የመብት ጥያቄና በተፈጠረው የወያኔ ጭፍጨፋ ምክንያት ከተለያዩ የክልሉ ዩኒቨርስቲዎች (ከሀሮማያ፣ ከጅማ፣ ከወለጋ … ዩኒቨርስቲዎች) የተያዙ ተማሪዎች እንዲሁም ከተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች (ከወለጋ፣ ከሞያሌ ወ.ዘ.ተ.) ተይዘው የታሰሩ ዜጎች በኦነግነት ተጠርጥረው በፌደራል የወንጀል ምርመራ ዘርፍ (ማዕከላዊ) የሚገኙ ሲሆን ክስ ሳይመሰረትባቸው ለበርካታ ወራት ያህል በወንጀል ምርመራ ዘርፍ ‘ማረፊያ ቤት’ ውስጥ ይገኙ ነበር።
ታዲያ ቃል በቃል ከምዕራቡ ዓለም የፀረ-ሽብርተኝነት ሕጎች ‘የተገለበጠው’ የኢትዮጵያ የፀረ-ሽብርተኝነት ሕግ እንዴት ቢሰራ ነው ሁሉንም የሕይወትና የኑሮ መስመሮች ‘በሽብርተኝነት’ ሊፈርጅ የቻለው? ወያኔ የሚጻረረውንና ለህልውናው አስጊ መስሎ የታየውን ማንኛውንም ግለሰብ ይሁን ድርጅት በተለይ የኦሮሞ ወጣቶችን፣ ጋዜጠኞችንና የተቃዋሚ ድርጅት መሪዎችን፣ አባላትና ደጋፊዎችን ማሰርና ማሰቃየት ሲፈልግ ስማቸውን ለማጉደፍ የሚጠቀምበት የተለመደ ተልካሻ ስልት እንዲህ በማለት ነው፣ “ጋዜጠኝነትን እና የፖለቲካ ድርጅትን ሽፋን በማድረግ የሀገሪቱንና የሕዝቦቿን ሰላም ለማደፍረስ ከሚያስቡና ከሚፈልጉ ‘ሀይላት’ ጋር ግንኙነት በማድረግ የተለያዩ የሽብር ተግባራትን ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ በቁጥጥር ስር አውለናቸዋል።” ይህ አይነት መሰረት የሌለው መግለጫ የኢትዮጵያ የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ጋዜጠኞችና በሰላማዊ መንገድ ተመዝግበው የፖለቲካ ምህዳሩን የተቀላቀሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት በወያኔ መራሹ የኢትዮጵያ መንግስት ከታሰሩ በኋላ በመንግስት አካላት የሚሰጥ የተለመደ አባባል ነው። የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት አምስት ዓመታት ውስጥም ከጋዜጠኛ እስከ ፖለቲከኛ፣ ከሀይማኖት መሪዎች እስከ ጦማሪያን፣ ከታጣቂ ወታደሮች እስከ ተራው ሰላማዊ ሰው … በዚሁ አዋጅ አማካኝነት ‘ሽብርተኝነታቸው ተረጋግጦላቸዋል’ ወይም ‘ይረጋገጥባቸው ዘንድ ፍርዳቸውን እየጠበቁ ይገኛሉ።’ ለመሆኑ ይህ ከ14 ዓመት ህፃን እስከ 80 ዓመት አዛውንት በሽብርተኝነት ወንጀል ክስ የሚያስቀጣው፣ ይህ ከታዋቂ ምሁራን እስከ ገበሬዎች ድረስ የሚያስረው … የወያኔ ሕግ በተጨባጭ ስፋትና ጥልቀቱ ምን ያህል ይሆን? ለታሪካዊ ጥያቄዎች ያለው ምልከታስ? በሀገሪቱ ስላለው የዲሞክራሲ ሁኔታስ ምን ይነግረናል? ስለ ጨቅላው የኢትዮጵያ ፌደራሊዝምስ ከፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉ ተግባራዊነት አንፃር ምን ይታየናል? ወ.ዘ.ተ. የሚሉትን ጥያቄዎች መሰረት በማድረግ በመሬት ላይ ያሉ የሕጉ እውነታዎችን በመመርመር ምልከታዎቹን በደንብ ማየትና እርምጃ ለመውሰድ በበቂ መዘጋጀት ያስፈልገናል።
ለእኛ የዲሞክራሲ ትርጉም ቢገባንም አምባገነኖች ግን ለፌዝና ለጨዋታ ስለሚጠቀሙበት በገዛ በቋንቋችን ነጻነት፣ ለውጥ፣ ፍትህ፣ ራስን በራስ ማስተዳደር እያልን እንዘምራለን፤ እንጮሃለን፣ ለለውጥ በጋራ በመነሳት ነጻነታችንን በትግላችን መቀናጀት ግድ ይለናል። በሃገራችን እና በነጻነታችን ላይ ባለቤቶች እንደሆንን ሃላፊነት ሊሰማን ስለሚገባ ነጻነታችንን ራሳችን ማረጋገጥ አለብን እንጂ የማንም ችሮታ እንዳልሆነ ተገንዝበን በጋራ ለለውጥ መነሳት ግዲታችን ነው። ነጻነታችን በእጃችን ስለሆነ ዛሪውኑ ለማስመለስ እንትጋ።

No comments:

Post a Comment