Wednesday, 12 November 2014

አማን ሄደቶ ቄረንሶ:- ተስፋዬ ገ/አብና የፓንዶራው ሳጥን – ክፍል አምስትና ክፍል ስድስት

በአማን ሄደቶ ቄረንሶ*
ክፍል አምስት
ደግ ሰው ትመስለኝ ነበር፡ ለካ ኦነግ ነህ!
ያለፉ ዝግጅቶችን ሃተታ አንዳንዶች ከአማራ ህዝብ ጥላቻ ጋር አያይዘውታል። ግልጽ መሆን ያለበት ነገር የአማራ ህዝብ በፍጹም! በተኣምር! የኦሮሞ ህዝብ ጠላት ሆኖ አያውቅም። ሊሆንም አይችልም። በአማራው ህዝብ ስም የሚነግዱ ወገኖች የሰሩት ግፍ የነዚያው ወገኖች ሃላፊነት እንጂ የአማራው ህዝብ አይደለም። በአንድ ወቅት አንድ የአማራ ተወላጅ ጓደኛ ነበረኝ። አማራ መሆኑን ያምናል። ኦሮሞ መሆኔን ያከብራል። “ኦሮሞ ነኝ” ስለው የማይናደድ ወይም የማያመው ሰው ነበር። እኔም እንደዚሁ። ወላጆቹ በኦሮሞ ህዝብ ላይ ያደርሱ የነበረውን በደል ያጫውተኝ ነበር። በልጅነቱ በሚሰሩት ስራ ከቤተሰቡ እንደማይስማማም ይነግረኝ ነበር። ከልቡ መሆኑ ደግሞ የበለጠ ጓደኛው እንድሆን አደረገኝ። ዛሬ የየኑሮአችን መንገድ ለይቶን ባንገናኝም ከልቤ ያልጠፋ ደግ ልጅ ነበር። ያለፉ ግፎች በስማቸው ለመጥራት ለምንታገል ሁሉ የአማራ ህዝብ ማለት እንደዚያ ጓደኛዬ ነው።
በአንጻሩ ደግሞ በራፋችን ላይ ቆመው “ኦሮምኛህን ቤትህ ገብተህ አውራ” የሚሉን ደፋሮች ዛሬም አሉ። አንድ ሰው ሊጠራበት የማይፈልገውን ስም “ብትጠራበት ምንድነው?” ብለው የሚከራከሩና ሳይቸግራቸው የሚቸገሩ ደረቆችን ዛሬም እያየን ነው። “ኢትዮጵያውያን ነን።” ይላሉ። “ጥርት ያልኩ አማራ ነኝ!” ይሉ በነበረበት ዘመን በነሱ የሚገረም አልነበረም። ዛሬ እኛ “ኦሮሞ ነን!” ስንል አብዮት ያውጃሉ። ኢትዮጵያ ማለት ለነሱ አማርኛ ብቻ የሚነገርባት፡ የቴዎድሮስና የምኒልክ ጀግንነት የሚሰበክባት፡ የ3000 ዘመናት አፈታሪክ የሚቀነቀንላት ጥንታዊት አገር! ለኛ ግን ኢትዮጵያ ማለት የዛሬ መቶ ከምናምን አመታት በጉልበት የተመሰረተችና ዛሬም ደም ደም የምትሸት፡ በደም በተቦካ አፈር ላይ የተተከለች፡ በጉልበት የታጨቁባት ህዝቦች ዛሬም ድረስ ዜጎቿ መሆን ያልቻሉባት፡ የአንዱ እናትና የሌላው የእንጀራ እናት ነች። በመቃብራችን ላይ የተገነባች! “የፓንዶራ ሳጥን! ተስፋዬ ገ/ዐብ ቁልፉን የነካካው የፓንዶራ ሳጥን!
በአንድ ወቅት በአንዱ የኦሮሚያ ከተማ፡ አንድ ትምህርት ቤት፡ አብረን ተምረን፡ ነገር ግን ተለያይተን ብዙ አመታት ከቆየን የአማራ ልጅ ጋር ተገናኝተን ሰላምታ ተለዋወጥን። ሁለታችንም በየፊናችን የህይወት ወከባ ስለነበረብን መልሰን ለመገናኘት ቀጠሮ ይዘን ተላለፍን። በቀጠሮአችን መሰረት ተገናኝተን ስለ ተለያዩ ጉዳዮች አንስተን ከተጨዋወትን በኋላ ዛሬም ተለያየን። ኋላ ላይ የመገናኘት እድሉ እየሰፋ ሄዶ በየጊዜው እንገናኝ ጀመር። አንድ ቀን ተገናኝተን ስናወራ በጫዋታ መሃል ስለ ፖለቲካ አንስተን ስንቀባጥር ሄደን ሄደን የኢትዮጵያዊነት ብሄራዊ ስሜት ጋ መጣን። ኢትዮጵያዊነት እንደሚያኮራው፡ ለኢትዮጵያዊነት ያለው ብሄራዊ ስሜት ልዩ እንደሆነ በጥሩ አማርኛ ጥሩ አድርጎ ሊያስረዳኝ ሞከረ። አስቀድሜ የማውቀው ቢሆንም በጣም በተለያዩ የአመለካከት አለማት ውስጥ ያለን መሆኑን የበለጠ ተገነዘብኩኝ። ትንሽ ካሰብኩ በኋላ “ታድለሃል!” ስለው የበለጠ ገለጻ ሊያደርግልኝ ተዘጋጀ። ግን አቋረጥኩት። “ይገርምሃል፡ በአመለካከት በጣም በሚራራቁ ጫፎች ላይ ነው ያለነው” ስለው “እንዴት?” አለኝ። “እንደምትለው የኢትዮጵያዊነት ብሄራዊ ስሜት ባንተ ውስጥ ልዩ ነው። እኔ ግን ስለ ኢትዮጵያዊነት የሚሰማኝ ስሜት የለም!” ስለው ፊቱ ተለዋወጠ። በዚያ ቅጽበት ሌላ ሰው የሆንኩ ያህል አትኩሮ ሲመለከተኝ ተመለከትኩት። “ይቅርታ! የማወራው የሚያስደስትህ እንዳልሆነ አስቀድሜ አውቃለሁ። ነገር ግን እውነታውን ከመናገር ውጭ አማራጭ የለኝም። ወደድንም ጠላን ኢትዮጵያ የተባለው አገር ተመስርቷል። ያኮራኛል የምትለው ኢትዮጵያዊነት ግን… ” አንጠልጥዬ ተውኩት። “እና?” አለኝ። “ጨርሻለሁ“ አልኩት። ትንሽ ካሰበ በኋላ ነገሩን ወደ ወያኔ አዞረው። እየተከዘ “አይ ወያኔ!” አለ። “ምነው?” ስለው “ጥሩ አድርጎ ኢትዮጵያዊነትን ውስጣችን ገድሏል” አለኝ። “በወያኔ አታመሃኝ። የምትለው ኢትዮጵያዊነት አልተመሰረተም!” ስለው “ወይኔ! ምንድነው የምታወራው? እየቀለድክ መሆን አለበት!” አለኝ። “ወንድሜ! ምንም ቀልድ የለም። የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ ቀድመው የፈረንጅ መሳሪያ የጨበጡ ጀብደኞች የዛሬ መቶ ከምናምን አመታት ገደማ ኢትዮጵያ የተባለችውን አገር በጠመንጃ ፈጥረው መሬቱን ከለሉ። አገራዊ ስሜት ግን በጠመንጃ ሃይል ተከልሎ የሚፈጠር አልነበረም። እንዲያም ሆኖ አገራዊ ስሜት ሊያመጡ ይችሉ የነበሩ ብዙ ተስፋዎች መክነዋል። ዛሬም የህዝቦች ማንነት ካልተከበረ ለዚህች አገር ያስፈራል” ስለው አሁንም ትኩር ብሎ እያየኝ “አንተም እንደ ወያኔዎቹ ነው የምታስበው?” ትንሽ ቆይቶም አከለ። “የኢትዮጵያን የረጅም ዘመናት የመንግስትነት ታሪክ ወደ መቶ አመታት ከሚሸበሽቡት ውስጥ ነህ ማለት ነው?” ሲለኝ ሳቄ መጣ። መልሼ “ወንድሜ! ትክክለኛ ስሜቴን ልንገርህ?” አልኩት። “አንተ የምትለው ኢትዮጵያዊነት ለኔ የዉሃ ጣእም ነው። ውስጤ የለም። ይሄን ደግሞ ከትግሬ ወደ ስልጣን መምጣት ጋር የሚያያይዘው ነገር የለም። ትግሬ ወደ ስልጣን ከመምጣቱ ሩቅ ዘመን በፊት ኦሮሞ ነበርን። ዛሬም ኦሮሞ ነን። ነገም ኦሮሞ እንደሆን እንቀጥላለን። እናም ውስጤ ያለው ኦሮሞነቴ ነው” አልኩት። የበለጠ ያሳቅሁት ግን በሚከተለው አባባሉ ነበር። “ወይኔ! ደግ ትመስለኝ ነበር። ለካ ኦነግ ነህ” አለኝ። አክሎም እንዲህ አለ። “የኦነግን ዘረኛ አመለካከት ታራምዳለህ ማለት ነው።”
በርግጥ አባባሉ “የአንድነት ሃይሎች ነን” ባይ ወገኖች ስለ ኦነግ ያላቸውን ስእል ሳያስታውሰኝ አልቀረም። ገዢ የነበሩ ሃይሎች በህዝቦች ላይ ይፈጽሙ በነበረው በደልና ግፍ የተፈጠረውን ኦነግ ከሌላ ክዋክብት (planet) የመጣ ጭራቅ አስመስለው ባገኙት ሚድያ ሁሉ ሲያብጠለጥሉ መኖራቸውን ሳነብና ሳዳምጥ የኖርኩ በመሆኑ እና ልጁ ደግሞ የነዚያ ወገኖች ጥላቻና ፍራቻ ሰለባ ከመሆኑ አኳያ አባባሉ አልገረመኝም። በአባባሉ እየሳቅሁ “በዚህ አገር በኦሮሞ ህዝብ ላይ ደርሶ የነበረውንና እየደረሰ ያለውን በደል የሚታገል ሁሉ ኦነግ የሚሆን ከሆነ፡ አዎን! ኦነግ ነኝ! ኦነግ የኦሮሞን ህዝብ ችግር የሚረዳ ከሆነ፡ እኔም ኦነግ ነኝ! አላፍርበትም! ስለ ማንነቴ ማንሳት፡ ስለደረሰብኝ በደልና ህመም መናገር ዘረኝነትን ማራመድ ከሆነም ዘረኛ ነኝ። ዘረኝነትን እኮራበታለሁ” ስለው “ጎበዝ ፖለቲከኛ ወቶሃል” ብሎ ካሾፈ በኋላ የተለመደውን የምንሊካውያንን አባባል ሰነዘረ። “ለነገሩ እኔ አልኩ እንጂ ኦነግ የታለ? ፖለቲካው ከስሯል። ደግሞም የኦሮሞን ህዝብ አይወክልም።” አለኝ። እኔን “ኦነግ ነህ” እያለ መልሶ ኦነግ አለመኖሩን ሲነግረኝ ሁለት የሚጣረሱ ሃሳቦችን እየተናገረ መሆኑን ያወቀ አይመስልም ነበር። ምክንያታዊነቱ ሳይሆን ስሜታዊነቱ ጎልቶ ይታይ ነበር። እሱ አለ እንጂ ኦነግ የታለ? በርግጥ የኢትዮጵያ አንድነት አቀንቃኝ ጸሃፊዎችም (በሙሉ ማለት ይቻላል) የሚከተሉት ስሜታቸውን ነው። በመሬት ላይ ያለውን እውነታ ይሸሹታል። ግን እያባረራቸው ነው። እንደጥላ በየሄዱበት ይከተላቸዋል። ሲደነብሩ ቀይ ብእር ያነሳሉ። ወይም ቀዩን ምላሳቸውን ይጠቀማሉ። ቀያይ ቃላትንም ይጽፋሉ ወይንም ይተፋሉ። እነዚያ ቀያይ ብእሮች ወይም ምላሶች ሄደው ሄደው ለዚያ አገር እየበጁ አይደለም።
ያ ጓደኛዬ ያንን ተናግሮኝ ተለየኝ። ከዚያ በላይ ቆሞ ሊከራከረኝ አልፈለገም ወይም አልቻለም። እሱ ከተለየኝ በኋላ የተናገረኝን መልሼ ሳስብ አሁንም ሳቄ መጣ። በርግጥ የዚያን ጓደኛ አባባል ሳስታውስ ከአመታት በኋላ ዛሬም እስቃለሁ። “ደግ ሰው ትመስለኝ ነበር። ለካ ኦነግ ነህ። ለነገሩ እኔ አልኩ እንጂ ኦነግ የታለ? ፖለቲካው ከስሯል። ደግሞም የኦሮሞን ህዝብ አይወክልም።” በርግጥ ኦነግ መኖሩን ለማረጋገጥ ተሰልፎ የጓደኛዬ ቤት በራፍ ድረስ መሄድ ያለበት አይመስለኝም። የኦሮሞ ህዝብም የኦነግን ድጋፍ ለመግለጽ መቶ ሃምሳ ቦታ መሰለፍ ያለበት አይመስለንም። የኦነግ ፖለቲካ የከሰረው ከኦሮሞ ህዝብ ጠላቶች አንጻር ብቻ መሆኑን ጓደኛዬም ሆነ መሪዎቹ ሊያውቁት ይገባል። እነሱ እንደሚሉት የኦሮሞ ህዝብ ኦነግን አይደግፍም እንበል።ኦነግም የኦሮሞን ህዝብ አይወክልም እንበል። ይሄን ማለታቸው አይደንቀንም። የሚደንቀን ግን “የኦሮሞ ህዝብ ባህሉን፡ ማንነቱንና ታሪኩን በጆሯችን መስማት የማንፈልገውን እኛን ነው የሚደግፈው” ከተባልን ግን ስቀንም አናባራም። በርግጥ እነሱ ይሄንንም አይሉም አይባልም። በአንድ ወቅት፡ ቢጨመቅ የኦሮሞ ደም የሚወጣውን አረንጓዴ፡ ብጫ፡ ቀይ የምኒልክ ባንዲራ የለበሱ አማሮች (የትሮይ ፈረሶች) “ኢትዮጵያውያን ኦሮሞች ነን!” ብለው “ማንንም ከመሆኔ በፊት መሆን የምችለው ኦሮሞ ነው!” ባለው ጃዋር መሃመድ ላይ ሰልፍ ወጥተው ነበር።
ይሁንና ከላይ ያነሳሁትን አባባል ተናግሮኝ ለተለዬኝ ጓደኛዬ ሳይለየኝ የሚከተለውን መልስ ባለመስጠቴ በወቅቱ ሳይቆጨኝ አልቀረም። “የህዝቦችን ማንነት ቆፍረው ሊቀብሩ ባይፈልጉ ኖሮ የኢትዮጵያ አንድነት አቀንቃኞች በሙሉ ደጋግ ሰዎች ናቸው”
(ይቀጥላል)
——————————-
ክፍል ስድስት
የሚሉሽን በሰማሽ…
በኢትዮጵያም ይሁን ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉ የ ”አንዲት ኢትዮጵያ” ብቸኛ ባለቤቶች እነሱ ከለመዱት ሃሳብ ውጭ የጻፈ ወይም የተናገረ ሁሉ ያንን አገር ሊያፈርስ የተነሳ ነው። ኢትዮጵያ የምትኖረው እነሱ ባሉት መንገድ ብቻ ነው። በርግጥ ኢትዮጵያን በአንድ ዘመን በራሳቸው መንገድ ብቻ አኑረዋታል። ያ ብቻ አይደለም። በፈላጭ ቆራጭ አገዛዛቸው ህዝቦችን አኖረውበታል። እንደፈለጉም ኖረውበታል። በአንድ ዘመን የነበረ አመለካከት ከጊዜ ጋር ራሱን ማስተካከል ካልቻለ መለወጡ አይቀርምና የነሱ አገዛዝ ጊዜውን ጠብቆ ተሸኘ። ያ ያለፈው ስረአት ገዳይ እንደነበረና ተመልሶ እንደማይመጣ ሲነገራቸው አብዮት ያውጃሉ። ጀዋር ሞሃመድ ምን ነበር ያደረገው? “ኦሮሞ ነኝ” አለ። የሚሰማውን እውነተኛ ስሜቱን ተናገረ። በቃ አብዮት ታወጀ። ከሚነግረን ኢትዮጵያዊነቱ ጀርባ በረዢሙ ቆሞ የሚያየን አማራነቱን የማናይ እየመሰለው ሊያጃጅለን የፈለገው ጋዜጠኛ አበበ ገላው “ጀዋር የጎሳ ብሄረተኛ ነው። እኔ ኢትዮጵያዊ ብሄረተኛ ነኝ “ ብሎ ሲያሾፍ ሰማን። በርግጥ ለሚለቀስላት ኢትዮጵያ የሚሻለው የሚያስመስለው ወይም የህዝቦችን መብት የሚቃወመው አበበ ገላው ሳይሆን እውነተኛ ማንነቱን የተናገረው ጀዋር መሃመድ ነው ብለን እናምናለን።
ስለ ኢትዮጵያ እውነተኛ ገጽታ ሲነገራቸው ጀዋር ላይ ያውጁት አብዮት የመጀመሪያው እንዳልነበረ ሁሉ የመጨረሻውም አልነበረም። በደራሲ ተስፋዬ ገ/አብ ላይ የታወጀው አብዮታቸው ደግሞ ሰንበትበት ብሏል። የተስፋዬ መነሻው የቡርቃ ዝምታ ነበር። የምኒልክ ወንጀል በ “የቡርቃ ዝምታ” ተነካ!! ቀጥሎም ከትልቁ የፓንዶራ ሳጥን “ጫልቱ እንደ ሄለን” የምትል አጭር ሰበዝ ተመዛ ታየችላቸው። በቃ! ሌላ አብዮት ተቀጣጠለ!! እነ ዳኛ ወልደሚካኤል መሸሻ የአለም አቀፉ ፍርድ ቤት አቃቤ ቢሆኑ ተመኙ። ለምን ሲባል ተስፋዬ ገብረአብን ህዝብን በህዝብ ላይ በማነሳሳት ወንጀል ሊከሱ። በርግጥ እነሱ የአለሙ ፍርድ ቤት ዳኛ አለመሆናቸው በጀን!! ቀልድ!
ከዚህ ቀደም እንዳልኩት የኢትዮጵያን ህልውና እየተፈታተነ ያለው የዚያ ያረጀና ያፈጀ አመለካከት ተሸካሚና ያ ስረአት ተመልሶ እንዲመጣ የሚመኝ እንደዚህ ያለ ህልመኛ መሆኑን አንስቼ ነበር። እኛ ያን ያለፈውን አመለካከታቸውን እንዲተውና ከዘመን ጋር ራሳቸውን እንዲያስተካክሉ ነው። አማራጭ ስለሌላቸው የህዝቦችን መብት እየመረራቸውም እንዲቀበሉ ነው። በርግጥ የጊዜው አቅጣጫ የገባቸው እንደነ ወጣት አቤኔዘር እየነገሯቸው ነው። መስማት ግን የሚችሉ አይደሉም። የዘሬን ከተውኩ ያንዘርዝረኝ ሆኖባቸው ነጋ ጠባ፡ ያንኑን የምኒልክ ህልማቸውን ያመነዥካሉ። ምኒልክ የሰራውን ኢፍትሃዊነት “ኢፍትሃዊነት” ብሎ መጥራት ለነሱ አይዋጥም ብቻ ሳይሆን ራሱም ኢፍትሃዊነት ነው። ያለፈውን የማይተው እነዚህ ወገኖች ያለፈውን እንድንተው ግን ይመክሩናል። አዎን! የምኒልክን ወንጀል ስናነሳባቸው እነሱው ወደፊት ተመልካች ሆነው “በምኒልክ ዘመን የተፈጸመውን ማውራት ዛሬ የሚጠቅመው ነገር የለም። ያለፈውን ትተን ወደፊት እንመልከት” ይሉናል። በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ይህን አባባል ያላነበብንበት ወይም ያላዳመጥንበት የአንድነት አቀንቃኞች ሚድያ የለም። ይህንን ባሉበት አንደበታቸው ወይም ብእራቸው መልሰው ስለ ምኒልክ ጀግንነትና ደግነት ያወሩልናል። የድርጅት ተወካይም ይሁን ግለሰብ ስለዚህ አሳምሮ ሲያወራ ከብዙ ጊዜ በላይ ሰምተናል። ለምሳሌ ያለፉትን ስረአቶች ተመልሰው እንዲመጡ የሚመኘውና በኢትዮጵያ አንድነት ስም የሚምለው የአማራ ብሄረተኛው ታማኝ በየነ ስለምኒልክ ጀግንነት፡ ደግነትና አርቆ አሳቢነት አውርቶ አይጠግብም። “የኢትዮጵያ ህዝብ ምኒልክን እምዬ ይላቸዋል” ብሎን ነበር በአንድ ወቅት። እዚህ ጋ ካነሳነው ርእስ ስለሚያስወጣን “ምኒልክን እምዬ’ የሚለው የኢትዮጵያ ህዝብ ማነው?” ብለን ታማኝን አንጠይቅም። እሱ የሚለው የኢትዮጵያ ህዝብ ማን እንደሆነ እንገነዘባለንና። እነዚህ ሰዎች ምኒልክን አይደለም መውደድ ማምለክ ይችላሉ። በተጨባጭ እየሰሩ ያሉትም ያንኑን ነው። ይሄን በማድረጋቸው አንገረምም። መብታቸው ነው። የምኒልክ ገዳይነት ለነሱ ጀግንነት ነው። ለዚህም አንታዘባቸውም። “ገዳያችሁ ምኒልክን አባታችን በሉት” ስንባል ግን ነገሩ ከማስገረምም በላይ ነው። እኛ ምኒልክን እንደነሱ እንድንወድ ብቻ ሳይሆን ጃግንነቱን ከነሱ ጋር እንድንዘምርና “አባታችን” ብለን እንድንጠራው ከሰበኩን (በርግጥ እየሰበኩም ነው።) ችግር ነው። ታማኝን ጨምሮ በሙሉ ማለት የሚቻል የአማራ ብሄረተኞች ምእራባዊው አትላንቲክ ውቅያኖስ አካባቢ የሚገኘውን ቤርሙዳ /የተባለውን ምስጢራዊ ክልል የሚያውቁትን ያህል ከአንድ ክ/ዘ/ በላይ በግፍ የገዙትን የኦሮሞን ህዝብ አያውቁትም።
በምሰራበት ቦታ “ምኒልክ!” የሚባል የስራ ባልደረባ አለኝ። ሰው ሲገናኝ መቸም የሚሰማውን ይናገራልና አንድ ቀን አንድ ኦሮሞ ጓደኛዬ ይህን የስራ ባልደረባችንን ስም ማን እንደሆነ ካረጋገጠ በኋላ “ይሄን ስም ይዘህ ወደ ሃረርና አርሲ አትውረድ” አለው። በአንድነት ፕሮፓጋንዳ የሚያደነቁሩን ወገኖች ምኒልክ እንኳን የፈጸማቸው ወንጀሎች ትክክለኛነት ማውራትና በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ስሙ ራሱ እንደወንጀል እንደሚታይ አያውቁም። ምኒልክ የገደላቸው ወገኖች መቃብር ላይ ቆመው ስለ ደግነቱና ጀግንነቱ ሊቦተልኩ ይፈልጋሉ። “አረ ይሄ ነውር ነው፡ ምኒልክ አራጃችን እንጂ ጀግናችን ሊሆን አይችልም” ስንላቸው “ምኒልክን በመጥላት የተለከፉ” ይሉናል። እነ ምኒልክን እንዴት አድርገን እንደምንወድ ግን አይነግሩንም። እኛ ኦሮሞች ችግራችንን ከምኒልክም ሆነ ከሌሎች ጨቋኝ ገዢዎች ጋር የማቆራኘት አራራ የለብንም። በሃበሻ ገዢዎች የደረሰብንን አብዛኛውን ረስተነዋል። እነሱው እያነሱ ተቸገርን እንጂ።
ግን እስቲ፡ ስለ ምኒልክ ጀግንነት የሚነግሩንን ታማኝና ጓደኞቹን አንድ ቀላል ጥያቄ እንጠይቃቸው። “ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስንና መምህር አሰፋ ማሩን የገደላቸው ማነው?” ብንላቸው፡ እነ ታማኝ፡ አፋቸውን ሞልተው “ይሄማ ምን ጥያቄ አለው? መለስ ዜናዊ ነዋ!” እንደሚሉን ጥርጥር የለውም። “አቶ መለስ ዜናዊ ለፕሮፌሰሩና ለመምህሩ ልጆች ጀግናና አባት መሆን ይችላሉ ወይ?” ብንላቸው ግን የእብድ ጥያቄ የጠየቅናቸው ያህል እንደሚገረሙም አንጠራጠርም። ትክክልም ናቸው። መለስ ዜናዊ ለፕሮፌሰሩና ለመምህሩ ልጆች ጀግናና አባት ሊሆን አይችልም። የአቶቻቸው ገዳይ እንጂ! ይሄን ጥያቄ አንስተን ወደ ምኒልክና ኦሮሞ ህዝብ ብናመጣው ግን የእነ ታማኝ መልስ የሚሆነው ሌላ ነው። ለነሱ መለስ ዜናዊ ገዳይ ነው። ምኒልክ ግን በነሱ አፍ በፍጹም ገዳይ አይሆንም። መለስ ዜናዊ ገዳይ የሚሆንበትንና ምኒልክ የማይሆንበትን ምክንያት ሊነግሩን አይችሉም። የመምህሩንና የፕሮፌሰሩን ግድያ ብቻ ሳይሆን በዚያ አገር በማንም ላይ የሚፈጸመውን ሰብአዊ ጥሰት ከልባችን እንቃወማለን። ነገር ግን ከላይ ላነሳነው ጥያቄ ከነሱ የምንሰማው የተለመደውን መልሳቸውን ነው። “ምኒልክ እጅና ጡት የቆረጠው ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ ነው።” የሚል ይሆናል። የምኒልክ ወንጀል የነሱ ምክንያት።
በሌላ በኩል እነዚህ ወገኖች በአሁኑ ወቅት የአኖሌን ሃውልት መቆም እየተቃወሙ ነው። ነገር ግን፡ የኦሮሞን እጅና ጡት የቆረጠው የምኒልክ ሃውልት ከኦሮሞ ምድር ይነሳ የሚለውን የኦሮሞ ጥያቄ እንዴት ይመልሱት ይሆን?? የአኖሌ ሃውልት የማያስፈልግ ከሆነ የምኒልክ ሃውልትም የሚያስፈልግበት ስነ አምክንዮ የለም። የሆነ ሆኖ፡ የአኖሌ ሃውልት አማራ ክልል አልተተከለም። በኦሮሞ ምድር ነው። “የኦሮሞ ህዝብ ለሚተክለውም ሆነ ለሚነቅለው ማንኛውውም ነገር የጎረቤቶቹን ፍቃድ አይጠይቅም!” ገዳ ገ/አብ። ለነዚህ ቡድኖች የሚሆን አጥጋቢ መልስ!
በመጨረሻ፡ “የሚሉሽን በሰማሽ…” ብለው የሚተርቱት እነሱ ናቸው። ተስፋዬ ገብረአብ ቁልፉን የነካካውን የፓንዶራ ሳጥን የመሰረተውን ምኒልክን የኦሮሞ ልጆች /ተማሪዎች/ ከሚሉት እስቲ አንዱን እንንገራቸው። ይጠይቃል አንዱ ተማሪ። “በ19ኛው ክ/ዘ/ እንጦጦ አፋፍ ቆሞ የኦሮሞን ደም በጀሪካን ይጠጣ የነበረው ሰው ስሙ ማነው ነበር?” “ይቺማ ቀላል ናት! ምኒልክ ነዋ!” ይላል መላሹ። በርግጥ ምኒልክ የኦሮሞን ደም በጀሪካን ሲጠጣ ያየው አልነበረም። ግነት ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ምኒልክ የኦሮሞን መሬት በደም ማጠቡ ወይም የኦሮሞን ጥቁር አፈር በደም ማጨቅየቱን፡ የኦሮሞን ጀግና እጅ፡ የኦሮሞን እናት ጡት መቁረጡን አይረሱትም። ታሪክ ነው። ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ ይኖራል። ከዚያም አልፎ፡ የኦሮሞ ልጆች ምኒልክን የሚመለከቱት እንደ አፍሪካዊው ሂትለር ወይም እንደ ጭራቅ ነው። “ሂትለር ለአይሁዳውያን አባትና ጀግና መሆን ከቻለ ምኒልክም አባታችን ሊሆን ይችላል” ይላሉ።
(ክፍል ሰባት ይቀጥላል።)
ቻው!

No comments:

Post a Comment