የአባ ሳሙኤል የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት በ1904 ዓ.ም. አቃቂ ወንዝ አካባቢ ተገንብቶ ሥራ መጀመሩን ሰነዶች ይጠቁማሉ፡፡
ኃይል ማመንጫው ሲያመነጭ የነበረውን 3.3 ሜጋ ዋት ኃይል ከዓመታት በፊት አቋርጦ የነበረ ቢሆንም፣ ከቻይና መንግሥት በተገኘው ዕርዳታ ታድሶ ኅዳር 8 ቀን 2007 ዓ.ም. የውኃ ሀብት፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ወንድሙ ተክሌና የኢትዮጵያ አሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አዜብ አስናቀ በተገኙበት ሥራው ተጀምሯል፡፡
አባ ሳሙኤል የኃይል ማመንጫ ጣቢያን የሚያድሰው ኃይድሮ ቻይና ኋዶንግ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የተባለው የቻይና ኩባንያ ሲሆን፣ እድሳቱ እንደተጠናቀቀ ኃይል የማመንጨት አቅሙ በእጥፍ አድጐ 6.6 ሜጋ ዋት እንደሚደርስም ተነግሯል፡፡
ኢትዮጵያ የህዳሴውን ግድብ በተፋጠነ ሁኔታ በራሷ ወጪ በመገንባት ላይ መሆኗን ያስታወሱት ወ/ሮ አዜብ፣ ለረጅም ዓመታት ማለትም ከ100 ዓመታት በላይ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቶ በብልሽት ምክንያት አገልግሎት መስጠት ያቋረጠውን አባ ሳሙኤል የኃይል ማመንጫ መታደሱ አጠቃላይ የኃይል ማመንጨት መጠንን ከፍ የሚያደርግ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
Source:: Ethiopian Reporter
No comments:
Post a Comment