Monday, 17 November 2014

ለስብሰባ ሲቀሰቅሱ የታሰሩት የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች 7 ቀን ተቀጠረባቸው • የሽብርተኝነት ክስ ቀርቦባቸዋል

(ነገረ ኢትዮጵያ) የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር ለህዳር 7/2007 ዓ.ም ጠርቶት ለነበረው የአደባባይ ህዝባዊ ስብሰባ አርብ ህዳር 5/2007 ዓ.ም በቅስቀሳ ላይ እንደነበሩ የታሰሩት የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች 7 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ተሰጠባቸው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ም/ሰብሳቢና የምርጫ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ አባል ወጣት ማቲያስ መኩሪያ እና የምርጫ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ አባል ወጣት ሳምሶን ግዛቸው በቅስቀሳ ወቅት ተይዘው አራዳ ፖሊስ መምሪያ የታሰሩ ሲሆን በዛሬው ቀን ችሎት ቀርበው የ7 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ ወጣቶቹ ‹‹ሽብር በማነሳሳት›› የሚል ክስ የተመሰረተባቸው ሲሆን ከታሰሩበት ጊዜ ጀምሮ በተለይ ሌሊት ደህንነቶች በተደጋጋሚ በኃይልና በዛቻ እንደሚመረምሯቸው ገልጸዋል፡፡
samson gizachew and matias mekuria
ታሳሪዎቹ ህጋዊ እውቅና ለተሰጠው ስብሰባ የቀሰቀሱ መሆኑን ጠቅሰው መታሰራቸው ህገ ወጥ በመሆኑ እንዲፈለቀቁ ቢከራከሩም፤ ፖሊስ ‹‹ሌሎች ግብረ አበሮቻቸው ስላልተያዙ መያዝ አለብን፡፡ እነሱም ከተለቀቁ መረጃ ያጠፉብናል፡፡›› በሚል የጠየቀው የ7 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ተቀባይት አግኝቷል፡፡ በአንጻሩ ታሳዎቹ የቀረቧቸው ቅሬታዎችና መከራከሪያዎች በዳኛዋ ተቀባይነት ሳያገኙ ቀርተዋል፡፡
አመራሮቹ እስካሁን ታስረው የነበሩት አራዳ ፖሊስ መምሪያ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በርካታ እስረኞች በአንድ ስር ቤት ውስጥ በሚታሰሩበት ወረዳ 9 እስር ቤት መዛወራቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሚያዚያ 19/2005 ሰማያዊ ፓርቲ ሰልፍ በጠራበት ወቅት ቅስቀሳ ላይ የነበሩ 41 ሰዎች ለ11 ቀን በህገ ወጥ መንገድ መታሰራቸውን ያስታወሱት የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት አቶ ዮናታን ተስፋዬ በአባሎቻቸው ላይ የተፈጸመው እስር የተለመደና የታቀዱት ስራዎችን ለመቀደናቀፍ ሆን ተብሎ የተደረገ እንደሆነ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ ኃላፊው ጨምረውም ‹‹ገዥው ፓርቲ ወጣቶች ከትግሉ እንዲርቁ ተመሳሳይ እርምጃ የሚወስድ ቢሆንም አባሎቻችን ቆራጥ በመሆናቸው አላማው አይሳካለትም›› ብለዋል፡፡ በተለይ በአሁኑ ወቅት በርካታ ስራዎችን የታቀዱ በመሆኑ ስራዎችን ለማደናቀፍ በርካታ አባላቶቻቸውን ሊያስር እንደሚችልም ግምታቸውን ገልጸዋል፡፡

No comments:

Post a Comment