በአምስት ወጣቶች ተደፍራ ህይወቷ ያለፈው ታዳጊ ሃና ላላንጎ ጉዳይ ከፍተኛ ቁጣን የቀሰቀሰ ሲሆን በተለያዩ የመገናኛ ብዙሀናትን ማህበራዊ ድረገፆች ላይ ድርጊቱን የፈፀሙት ግለሰቦች ተይዘው የሀገሪቱ ህግ ያስቀመጠው ከፍተኛ ቅጣት በአፋጣኝ እንዲፈረድባቸው እየተጠየቀ ነው፡፡
በተለያዩ ማህበራዊ ድረገፆች፤ “ፍትህ ለሃና” የሚል ንቅናቄ የተጀመረ ሲሆን በተለይ ተጠርጣሪዎቹ ረቡዕ ህዳር 10 ቀን 2007 ዓ.ም ፍርድ ቤት ቀርበው “ድርጊቱን የፈፀምነው እኛ አይደለንም፣ ለፖሊስ ድርጊቱን ፈፅመናል ብለን ቃል የሰጠነው ተገደን ነው ፈፃሚዎችን እንጠቁም” ማለታቸውን ተከትሎ የፍትህ አካላት ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡ የሚጠይቁ ወገኖች ተበራክተዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ አስተያየት የጠየቅናቸው የህግ አማካሪና ጠበቃ አቶ ጳውሎስ ተሰማ እንዳብራሩልን፤ በወንጀለኛ መቅጫ ህግ በአንቀፅ 620 ንኡስ ቁጥር 1 መሰረት፤ “በግብረስጋ ግንኙነት ነፃነት እና ንፅህና ላይ የሚፈፀም ወንጀሎች” ብሎ በአስገድዶ መድፈር ርእስ ስር “ማንም ሰው ሀይል በመጠቀም ወይም በብርቱ ብቻ የሚፈፀም ድርጊት ወይም ህሊናዋን እንድትስት በማድረግ ወይም በማናቸውም መንገድ እራሷን መከላከል እንዳትችል በማድረግ ከጋብቻ ውጪ አስገድዶ ከአንዲት ሴት ጋር ግብረ ስጋ ግንኙነት የፈፀመ እንደሆነ ከ5 ዓመት እስከ 15 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ይቀጣል” የሚል ሲሆን በአንቀፅ 620 በንዑስ ቁጥር 2 ላይ እድሜዋ 18 ዓመት ባልሞላት ሴት ልጅ ላይ የአስገድዶ መድፈር በሚፈፀምበት ጊዜ የግል ተበዳይ በተከሳሹ ቁጥጥር ስር በምትገኝበት ወይም በሱ ጥገኛ በሆነች ጊዜ ቅጣቱ ከ5 ዓመት እስከ 20 ዓመት ድረስ ይሆናል፡፡
ታዳጊዋን ለስራ የተሰማሩ መስለው ሲንቀሳቀሱ በታክሲው ተሳፍራ በቁጥጥራቸው ስር እንድትሆን በማድረግ ወንጀሉን በህብረት የፈፀሙባት በመሆኑ ቅጣቱ ከ5 ዓመት እስከ 20 አመት ይደርሳል፡፡ አስገድዶ መድፈሩ በተበዳይ ላይ የሞት አደጋ ያስከተለ እንደሆነ ከላይ በጠቀስነው የወንጀለኛ መቅጫ ህግ፤ ቅጣቱ እድሜ ልክ እስራት ይሆናል፤” ያሉት ጠበቃው፤ “በታዳጊዋ ላይ የተፈፀመው ወንጀል ከአንድ በላይ በመሆን ጭካኔ በተሞላ ሁኔታ በቁጥጥራቸው ስር በምትገኘው ለአቅመ አዳም ያልደረሰች ልጅ ላይ በመሆኑ በዕድሜ ልክ እስራት ይቀጣሉ” ብለዋል፡፡ ተደራራቢ ቅጣቶች አቃቤ ህግ ከከፈተ ቅጣቱን ሊያከብደው ይችላል፤ ነገር ግን የአስገድዶ መድፈር ህግ ላይ ከእድሜ ልክ እስራት በላይ የተቀመጠ ነገር የለም ሲሉ አስተያታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በሌላ በኩል የኢፌዲሪ ሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ በሰጡት መግለጫ፤ ድርጊቱን የፈፀሙትን ግለሰቦች ለፍርድ ለማቅረብ ጠንክሮ እንደሚሰራ አስታውቆ፤ በሰብአዊ ፍጡር ላይ ኢ-ሰብአዊ ጥፋት የሚፈፅሙ የሰው አራዊቶች ከህግ በላይ አይሆኑም ብሏል፡፡
አየር ጤና በሚገኘው ታይምስ ኢንተርናሽናል ትምህርተ ቤት የ10ኛ ክፍል ተማሪ የነበረችው የ17 ዓመት ታዳጊ ሀና ላላንጎ፤ አየር ጤና በተለምዶ ሳሚ ካፌ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ በሚኒባስ ተሳፍራ ወደ ጦር ኃይሎች መስመር በመሄድ ላይ እንዳለች በሚኒባሱ ውስጥ በነበሩ አምስት ወንዶች ታፍና ተወስዳ፣ በተፈፀመባት አስገድዶ መድፈር በደረሰባት ከፍተኛ ጉዳት በዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ህክምና በመከታተል ላይ ሳለች ህይወቷ ማለፉ የሚታወስ ሲሆን ድርጊቱን ፈፅመዋል የተባሉት ተጠርጣሪዎች ፍርድ ቤት ቀርበው ድርጊቱን አልፈፀምንም ብለው ክደዋል፡፡ ፍ/ቤትም ጉዳዩን ለህዳር 22 ቀን 2007 ዓ.ም ቀጥሯል፡፡
No comments:
Post a Comment