ቦሩ በራቃ | Bitootessa 15, 2015
የቅማንት ህዝብ በኢትዮጵያ ኢምፓየር ውስጥ ታሪካዊና ጥንታዊ ህዝብ ነው። ይህ በጎንደር ውስጥ የሚገኝ ህዝብ ከኩሽ ነገድ የሚመደብ ሲሆን ከታላቁ የኣገው ህዝብ ጋር ጥብቅ የሆነ የደም፣ የቁዋንቁዋ፣ የባህልና ባጠቃላይ ጠንካራ የማንነት ትስስር ያለው ህዝብ ነው። ቅማንቶች ጥንት ከኣገው ህዝብ ጋር ብሄራዊ ኣንድነት የነበራቸውና በጊዜ ሂደት ራሳቸውን ችለው ወደ ቅማንት ብሄርነት እንዳደጉ ታሪክ ያስረዳል። የሚኖሩትም ጎንደር ውስጥ በሚገኙ ቢያንስ በ6 ወረዳዎች ማለትም ጭልጋ፣ ላይ ኣርማጮሆ፣ መተማ፣ ቁዋራ፣ ደምቢያና ወገራ መሆኑን ጥናቶች ያመለክታሉ። ጎንደር ከተማና ዙሪያው ራሱ የቅማንት ህዝብ ሲኖርበት የነበረ መሬት መሆኑም ይነገራል።
ቅማንቶች ለበርካታ ክፍለ ዘመናት በኣማራ ብሄር ተውጠው የኖሩ በመሆኑ በኣብዛኛው ማነንታቸው ተመናምኖ ወደመሞት ደረጃ ተቃርቦ እንደነበር የብሄረሰቡ ተወላጅ የሆኑ ምሁራን ይናገራሉ። ዛሬ እንደ ወሎዬው ኣማርኛ ተናጋሪ ኦሮሞ ሁሉ ኣብዛኛው የቅማንት ተወላጅ ኣማርኛና ትግርኛ ተናጋሪ ከመሆኑ የተነሳ ጥቂት የማይባሉትም ራሳቸውን በኣማራነት የሚገልጹ ናቸው። እ ኤ ኣ በ1994 በተደረገው የቤትና ህዝብ ቆጠራ መሰረት የቅማንት ህዝብ ኣጠቃላይ ብዛት ከ170,000 በላይ መሆኑ ተመዝግቦ ነበር። ቅማንትኛን መናገር የሚችሉት ደግሞ 1625 ኣንደሚደርሱ ተለይቶ ነበር።
ይሁን እንጂ ከ13 ኣመት በሁዋላ 2007 ላይ በተደረገው የቤትና ህዝብ ቆጠራ ወቅት በሚገርም መልኩ ቅማንት እንደ ቅማንትነቱ ሳይቆጠርና የህዝቡ ቁጥርም ሳይዘገብ ታልፏል። በዚህ ወቅት ቢያንስ ከ500,000 በላይ መሆን የሚችለው የቅማንት ህዝብ ቁጥር በኣማራነት ተውጦ የኣማራን ህዝብ ቁጥር ከፍ ኣደረገ። የቅማንት ብሄረሰብ ደሞ ብሄረሰባዊ ህልዉናው እንደገና ታፈነ። ይህም በብሄረሰቡ ተወላጅ ምሁራን ዘንድ ከፍተኛ ቅያሜና ቁጣ እንዲቀሰቀስ ምክንያት ሆኗል። የወያኔ መንግስት የብሄር ማንነት ላይ የተመሰረተ የፌደራሊዝም ስርኣት ዘርግቻለሁ እያለ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ቅማንትን በቅማንትነቱ ማወቅ ኣልፈለገም። ዛሬም ቢሆን በጥቂቱም ቢሆን እንዲያውቅ ያስገደደው መንግስታዊ ሃላፊነት ተሰምቶት ሳይሆን የብሄረሰቡ ተወላጆች ያነሱት የመብት ጥያቄ ነው።
በቅማንት ህዝብ ላይ ከፍተኛ ጭቆና እያደረሰ ያለው የኢህኣዴግ ኣካል የሆነው ብኣዴን ራሱ መሆኑን የቅማንት ብሄርተኞች በምሬት ይናገራሉ። ብኣዴን ቅማንት የሚባል ብሄር የለም እስከ ማለት ድረስ በመሄድ የብሄረሰቡን ማንነት የሚያፍነው ሲወርድ ሲዋረድ በመጣው የኣማራ ትምክህተኝነቱ ጸንቶ መሆኑ ይታወቃል። በክልሉ ውስጥ የሚገኙትን የሌሎች ኣናሳ ወገኖች ማንነት በሃይል ጨፍልቆ ወደ ኣማራነት ማጠቃለል ዛሬም የቀጠለ መሆኑን ከዚህ መረዳት ይቻላል። ባለፉት ክፍለዘመናት በፊውዳል ነፍጠኞች የኣፈና ስርኣት ሳቢያ ጋፋት የሚባል ብሄር እስከነ ቁዋንቁዋው ጠፍቷል። ቅማንት ከሞት ኣፋፍ ኣገግሞ ማንነቱን እያንሰራራ እንደሚገኝ ሁሉ ኣማራው ምድር ላይ ለሞት የተቃረቡት እነዛ ጥንታዊ ብሄረሰቦችም ዳግም ይነሱ ይሆናል።
በጣም የሚገርመው ደግሞ ከወያኔ መንግስት በባሰ መልኩ ‘እምዬ ኢትዮጵያ’ እያሉ የኣዞ እምባ የሚያነቡት በስመ ተቃዋሚነት የተሰለፉ የኣገር ውስጥና የውጭ ተቃዋሚ ድርጅቶች ናቸው። እነዚህ በትምክህተኛ የነፍጠኛ ልጆች የሚመሩት ድርጅቶችና ደጋፊዎቻቸው የቅማንትን ህዝብ እሮሮ መስማት ከቶ ኣይፈልጉም። እንዲያውም ቅማንት የሚባል ብሄር ኣማራው ኣገር ውስጥ የለም እስከማለት የደረሱ ናቸው። ከዚህም የተነሳ ዛሬ ኣገር ቤትም ሆነ በዳያስፖራው ከሚገኙ ኣፍቃረ-ነፍጠኛ የዜና ኣውታሮች ኣንዳቸውም ስለቅማንት ህዝብ ብሶት ቃል ሲተነፍሱ ኣይሰሙም። ዛሬም የኣንድ ህዝብ ድምፅ እንዳፈኑ መቀጠል የሚቻል እየመሰላቸው ዝምታን መምረጣቸው የሚያስተዛዝብ ነው።
እውነትና ንጋት እያደር ይጠራል እንዲሉ ዛሬ የቅማንትን ህዝብ ማንነት መካድ ከማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል። ይህ ህዝብ ኣሁንስ መረረኝ በቃኝ ጭቆና ብሎ ተነስቷል። ትግሉ በሚገርም ፍጥነትም ወደፊት እየገሰገሰ ነው። በኣገሪቷ ዩኒቨርሲቲዎች የሚያስተምሩና የሚማሩ የቅማንት ተወላጅ ምሁራን በኣጭር ጊዜ ውስጥ በመደራጀት ባሳዩት የትግል ቁርጠኝነት የታፈነውን ድምጻቸውን ማሰማት ጀምረዋል። በዚህም መሰረት ለስርኣቱ ባቀረቡት ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ በጥቂቱም ቢሆን ምላሽ ተሰቶኣቸዋል። ይሁን ኣንጂ የወያኔ መንግስት ቅማንቶች በ126 ቀበሌዎች ላይ ካነሱት የይገባኛል ጥያቄ 42ቱን ብቻ ፈቅዶ የተቀሩትን 84ቱን ቀበሌዎች በመንፈጉ ትግሉ ይበልጥ እንዲፋፋም ኣድርጎታል።
ቅማንቶች ኣንዴ ተነስተናል ወደሁዋላ ማለት የለም ብለዋል። የጀመርነውን ትግል በ3 እጥፍ ኣሳድገን እንቀጥላለን እያሉም ናቸው። በርግጥ መቀጠልም ይችላሉ። ኣማራ ኣይደለንም ቅማንት ነን ካሉ መብታቸው መከበር ኣለበት። ለበርካታ ክፍለዘመናት ትምክተኝነት በነገሰበት ምድር ላይ የራሳቸውን ማንነት ከሞት ኣትርፈው ከዛሬ የደረሱ ጀግኖች እንደመሆናቸው መጠን ዛሬ የተቀረውን የትግል ጉዞ በድል ኣጠናቅቀው ሙሉ መብታቸውን የማያረጋግጡበት ምንም ምክንያት የለም። በብሄር እኩልነት የማያምኑ ትምክህተኞች በሰው ኣገር ላይ ውር ውር እያሉ የታሪክን ጎማ ወደ ሁዋላ ለመጠምዘዝ ከሚደክሙ እዛው ኣገራቸው መሃል ለተነሳው የፖለቲካ ትኩሳት በጊዜ ኣዎንታዊ መፍትሄ ቢፈልጉለት የተሻለ ነበረ። ጊዜ ያለፈበትን የእናውቅልሃለን ፈሊጣቸውን ከጉያቸው ስር ኣውጥተው በመጣል እውነትን ኣምኖ የመቀበያው ጊዜ ደርሷል።
የቅማንቶች ጥያቄ ሰፊውን የኣማራ ህዝብ መዳፈር ወይም መብቱን መጋፋት ኣይደለም። በታሪካዊውና ጥንታዊ ኣገራቸው ላይ ነው የይገባናል ጥያቄ ያነሱት። የኣማራ ህዝብም የዚህን ጥያቄ ፍትሃዊነት ተገንዝቦ ከወንድሙ የቅማንት ህዝብ ጎን መሰለፍ ኣለበት ኣንጂ በኣወናባጅ ትምክህተኞች ተወናብዶ ጥላቻ ማሳየት ኣይጠበቅበትም። ተማርን እያሉ ከጣራ በላይ ኣየጮሁ ዛሬም በትምክህት ኣስተሳሰብ ተወጥረው የሌላውን ህዝብ ማንነት ማፈን በሚፈልጉት ጠብ ኣጫሪ ወገኖቹ ኣማራው መታለልና መደናገር የለበትም። የየራስን ማንነት ኣውቆ ተከባብሮ ኣብሮ መኖር የስልጣኔ ምክልት ነው።
የቅማንት ብሄረሰብ የማንነት ጥያቄ በሁሉም የኣገሪቷ ነጻነት ናፋቂ ህዝቦች ዘንድ መደገፍ ያለበት ጥያቄ ነው። ኦሮሞው፣ ኣፋሩ፣ ሲዳማው፣ ሶማሉ፣ ቤኒሻንጉሉ፣ ጋምቤላው ራሱ ኣማራው ወዘተ የቅማንቶችን ብሶት እንደራሱ ብሶት ቆጥሮ የትግል ኣጋርነቱን ማሳየት ይጠበቅበታል። በተለይም የኦሮሞ ምሁራንና ብሄርተኞች በኣገሪቷ ባላቸው የብዙህነት ልክ ለቅማንት ህዝብ ያልተቆጠበ ድጋፍ የማድረግ ሃላፊነት ኣለባቸው። በኣገሪቷ ከፍተኛ የትምህርት ተቁዋማት የሚማሩ የኦሮሞ ተማሪዎች ከቅማንት ተወላጅ ተማሪዎች ጋር ያላቸውን ታሪካዊ ዝምድና በማደስና መረጃ በመለዋወጥ የጋራ ትግላቸውን ማቀናጀት ጠቃሚ ነው። የኢትዮጵያ ገዢ መንግስታት ጭቆና ሰለባ የነበሩትና ዛሬም ቢሆን ከጭቆናው ያልተላቀቁት ህዝቦች በሙሉ ተመሳሳይ እጣ ፈንታ ያላቸው እንደመሆኑ መጠን የቅማንት ህዝብ ለነጻነቱ የሚያደርገውን ትግል በተቻላቸው ኣቅም ሁሉ መደገፍ ኣስፈላጊ ይሆናል።
No comments:
Post a Comment