Saturday, 20 December 2014

MUST-READ | ቦሩ በራቃ:- የፀሃዬ ዮሃንስ ኣዲስ ዜማ – ‘Bishan Qabbanaa’ | ቀበና

በቦሩ በራቃ*
እነሆ ለዘመናት የምናውቀው ዝነኛው ድምጻዊ ፀሃዬ ዮሃንስ እጅግ ድንቅ መልእክት ያዘለ የኣፋን ኦሮሞና ኣማርኛ ቅልቅል ዜማ ጀባ ብሏል። ፀሃዬ በኣፋን ኦሮሞ ሲያዜም ታድያ ዝም ብሎ ተራ ግጥም ኣይደለም የተጠቀመው። ‘Bishan Qabbanaa’ በሚል ርእስ የዘፈነው ይህ ዘፈን በኣማርኛ ኣርቲስቶች የጥበብ ስራ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያውን ኣሻራ ኣኑሯል። ፀሃዬ የኣማርኛ ድምጻዊያንን ታቡ (taboo/ነውር) በመስበር በቀበና ወንዝ ስም ኣስታክኮ የፊንፊኔን የኦሮምያ እምብርትነት ነው ለዛ ባለው ድምጹ ያንጎራጎረው። የሚገርመው ፀህዬ በዚህ ዜማው ስለ ቀበና ወንዝና ስለ ሸገር ልጅነቱ ሲያወሳ ኣንድም ቦታ ላይ ‘ኣዲስ ኣበባ’ ብሎ ኣልጠቀሰም። ጨዋታው ገብቶታል። ይህ ቀላል ነገር ኣይደለም።
አኔ አስከማውቀው ድረስ አንደ ፀሃዬ ዮሃንስ ለ‘ኢትዮጵያዊነት’ ፍቅር መስዋእትነት የከፈለ የኣማርኛ ድምጻዊ የለም። ይሄን የምለው ፀሃዬ ዛሬ የኦሮሞን የኣገር ባለቤትነት መብት የሚደግፍ ዜማ በኣፋን ኦሮሞ ስላዜመ ብቻ ላንቆለጳጵሰው ኣይደለም። ፀሃዬ ከኤርትራ ነጻነት በፊት በነበረችው የኢትዮጵያ ኣንድነት በፅኑ የሚያምን ኣርቲስት እንደነበረ ኣውቃለሁ። ምንም ኣንኩዋን ቤተሰቦቹ ከኤርትራ ቢሆኑም ፀሃዬ ከኤርትራ ነጻነት በሁዋላ ኤርትራን ረግጦ የሚያውቅም ኣይመስለኝም። እንዲያውም ባንድ ወቅት ኣስመራ ላይ እንደሰማሁት ከሆነ ፀሃዬ እናቱ ሸገር ውስጥ በደረሰባቸው የመኪና ኣደጋ ኣርፈው ኣስከሬናቸው ወደ ኣስመራ ሲሸኝ ኣስከ እስመራ ድረስ ኣስከሬናቸውን ኣጅቦ በመሄድ ሊቀብራቸው ፈቃደኛ ኣልነበረም። የወላጅ እናቱን ኣስከሬን ቦሌ ኣይሮፕላን ጣቢያ ላይ ቆሞ ኣልቅሶ ከመሸኘት ውጪ ወደ ኣስመራ ለማቅናት እግሩን እንዳላነሳ ነው የሚነገረው። ፀሃዬ በሪፈረንደሙ ወቅት የኢትዮጵያዊነት ፍቅር ስላመዘነበት የኤርትራን ነጻነት ባለመደገፉ ኤርትራ ለመሄድ ችግር እንደነበረበት ይነገራል። የኢትዮጵያዊነት ፍቅር እስከዚህ ድረስ መስዋአትነት ኣስከፍሎታል።
ይህን ያነሳሁት ያለምክንያት ኣይደለም። ፀሃዬ ዮሃንስ ከልጅነቱ ጀምሮ በ’ኣውነተኛ’ የኢትዮጵያዊነት ፍቅር ነው ያደገው። በዘፈኖቹ ሁሉም ይህንን ኣስመስክሯል። በተለይም እንደ ግእዝ ኣቆጣጠር በ1982 ‘ተባለ እንዴ’ በሚል ርእስ በለቀቀው ኣልበሙ ውስጥ ‘ማን ኣንዳገር’ እያለ ያንጎራጎረው ዜማ ለኣብነት የሚጠቀስ ነው። በቅርቡ ደግሞ ወላይታና የደቡብ ህዝቦችን በፍቅር የሚያወድስ የሙዚቃ ስራ ኣበርክቶ ነበር። ፀሃዬ የተወለደበትን ብሄርም የሚረሳ ኣርቲስት ኣለመሆኑን ልክ እነ ጥላሁን ገሰሰ፣ ብዙነሽ በቀለ፣ ሃመልማል ኣባተና ሌሎችም በኣፋን ኦሮሞ እንደሚያደርጉት ሁሉ በሚለቃቸው ኣልበሞቹ ሁሉ ኣንዳንድ የትግርኛ ዘፈኖችን ጣል እንደሚያደርግ ይታወቃል። ለርሱ ኢትዮጵያ ማለት የትምክህተኝነት የበላይነት ሳይሆን የልዩነት ኣንድነት መሆኗን የኣርት/Art ስራዎቹ እየመሰከሩ ነው።
ፀሃዬ ኣሁን በኣፋን ኦሮሞ ቅልቅል የሰራው ዜማ ግን በግጥም ይዘቱ ልዩና ኣስገራሚ ነው። ለጊዜው የግጥሙ ደራሲ ማን እንደሆነ ባናውቅም ፀሃዬ ራሱ ኣስቦ ይህንን ኣይነት ግጥም መጠቀም እንደፈለገ ግን ለመገመት ኣያዳግትም። በግጥሙ ውስጥ፣
‘Beenaa ni deemnaa bishaan Qabbanaa 
Maaliif guggubannaa
Of qabbaneeffannaa’
ብሏል። በዚህ ኣባባሉ ኦሮሞ በገዛ ኣገሩ ኣምብርት ላይ ሆኖ ያደረበትን የጭቆና ትኩሳት መስክሯል። የተለያዩ የፊንፊኔ የሰፈር ስሞችን እየጠቃቀሰም ከቀበና ጋር በማስተሳሰር የፊንፊኔን የማይካድ ኦሮሞነት በግልጽ ቁዋንቁዋ ተርኮኣል።
‘በጋም ሆነ ክረምት በጸሃይ ዳመና
ከዚህም ከዚያም መጥተን ዋኝተናል ቀበና’
ሲልም ማናቸውም የፊንፊኔ ተወላጅ ነዋሪዎች የቀበና (ፊንፊኔ) ማእድ ተቁዋዳሾች መሆናቸውን ያስታውሳቸዋል።
‘ፍቅር ኣጠራርቶን ከፈረንሳይ ቤላ
ቀበና ታደምን ከኣዋሬ እስከ ሾላ
ምንም ብንራራቅ ቢለያይ ደብራችን
ከማዶ እስከማዶ ኣንድ ነው ወንዛችን’
ሲል ልዩነታችንና የማንነት መብታችን ሳይጨፈለቅ ተከባብረን በፍቅር መኖር እንደምንችል መክሯል። በዚህ ስንኝ ውስጥ ፀሃዬ ‘ቢለያይም ደብራችን ኣንድ ነው ወንዛችን’ ማለቱ ጥራዝ ነጠቆቹ እነ ቴዲ ኣፍሮ ‘ኣንድ ነው ደማችን’ ያሉትን የብሄር ማንነት ጭፍለቃ ለማረም የፈለገም ይመስላል።
የሚገርመው ደግሞ ፀሃዬ ለዜማው ኣርእስትነት የተጠቀመው ቀበና በኦሮሞ ህዝብ የነጻነት ትግል ሂደት ውስጥም ታሪካዊ ሰፈር ነው። በሽግግር መንግስቱ ወቅት የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር የነበሩት ኦቦ ኢብሳ ጉተማ: “Prison of Conscience” በሚለው መጽሃፋቸው ገጽ 138 ላይ እንደገለጹት የኦሮሞ ታጋዮች በ1976 የመጀመሪያውን የኦነግ የፖለቲካ ፕሮግራም ለማሻሻል ጉባኤ የተቀመጡት እዚሁ ቀበና ወንዝ ኣካባቢ እንደነበረ ነው።
ይህ የፀሃዬ ለየት ያለ ስራ ምናልባት ከበርካታ ግትር ትምክተኞች ዘንድ ሃይለኛ ነቀፌታና ጥላቻ ሊጋብዝበት እንደሚችል ይገመታል። በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ደግሞ ታሪካዊ ሰው ሊያስብለው ኣቅም ኣለው። በተለይም የወያኔ መንግስት የፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሞ መሬቶችን ለመንጠቅ ኣደገኛ ዘመቻ በተያያዘበት በዚህ ወቅት ፀሃዬ ኣይደለም የፊንፊኔ ዙሪያ ታላቁዋ ፊንፊኔ ራሷ ኦሮሞ መሆኗን በኣፋን ኦሮሞ መመስከሩ በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ የሚያስመሰግነው ስራ ነው። ፀሃዬ የቀደደውን ኣዲስ የጥበብ ፈር ሌሎችም እንደሚከተሉት ተስፋ እናደርጋለን።

No comments:

Post a Comment