Wednesday, 24 December 2014

‹‹ለዜጎች ጥያቄ ጥይት መፍትሔ አይሆንም›› ብለዋል

በባህር ዳር ተቃውሞ የአንድ ሰው ሕይወት ብቻ ማለፉን ፖሊስ ገለጸ -ተቃዋሚ ፓርቲዎች
bahrdar 3በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መቀመጫ በባህር ዳር ከተማ ሙሉዓለም የባህል አዳራሽ አካባቢ የሚኘውን መንገድ ለማስፋት፣ የከተማው መስቀል አደባባይ አንድ ሜትር ተኩል ይፈርሳል በመባሉ ተቃውሞ አደባባይ ከወጡ በርካታ ሰዎች ውስጥ ጉዳት የደረሰባቸው ጥቂቶች መሆናቸውንና የአንድ ወጣት ሕይወት ማለፉን ፖሊስ ገለጸ፡፡
የከተማዋ ፖሊስ ሰሞኑን ለመንግሥት የመገናኛ ተቋማት እንደገለጸው አንድ ወጣት በደረሰበት ጉዳት በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ ሕይወቱ ማለፉንና በዚህም ሐዘን እንደተሰማው ገልጿል፡፡
ይሁን እንጂ ሞተ የተባለው ወጣት በጥይት ተመትቶ ይሁን አይሁን አልገለጸም፡፡ በአካባቢው የሚገኙ የሪፖርተር ምንጮች የሟቾቹ ቁጥር ሦስት መሆኑንና በርካታ ወጣቶች፣ ሴት አዛውንቶችን ጨምሮ ጉዳት እንደደረሰባቸው ይናገራሉ፡፡
የከተማው አስተዳደር መንገዱን ለማስፋት ዕቅድ አውጥቶ መንቀሳቀስ የጀመረው ከአካባቢው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አመራሮች ጋር ተወያይቶና ይሁንታ አግኝቶ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ይህንን ያልተቀበሉና ያልሰሙ ምዕመናን በከተማዋ እምብርት ከሚገኘው ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በመነሳት፣ ወደ ከተማው አስተዳደር ምክር ቤት በኃይል ለመግባት መሞከራቸውን ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል ፖሊስ ተቃውሞውን በጥይት ለማብረድ መሞከሩ ያልሠለጠነ ዕርምጃ ነው በሚል ተቃውሞ እየገጠመው ይገኛል፡፡ የዘጠኙ ፓርቲዎች ትብብር ታኅሳስ 13 ቀን 2007 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ባወጣው መግለጫ ‹‹ለሰላማዊ ዜጎች ጥያቄ ጥይት መፍትሔ አይሆንም፤›› ሲል በባህር ዳር ከተማ ተቃውም የደረሰውን ጉዳት ተቃውሟል፡፡
ፖሊስ በጥይት በወሰደው ዕርምጃም የአምስት ዜጎች ሕይወት ማለፉንና በርካቶች በተለይም አዛውንቶች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል ሲል በመግለጫው ገልጿል፡፡
ድርጊቱንም ‹‹የልማት ሥራ ሕዝብን በማሳመን ብቻ የሚከናወን መሆኑ ያልገባቸው አምባገነን ባለሥልጣናት ዕርምጃ ነው፤›› ብሎታል፡፡
በአቶ አየለ ጫሚሶ የሚመራው ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ የኦርቶዶክስ ምዕመናን ለጠየቁት ሃይማኖታዊና መንፈሳዊ ጥያቄ በጦር መሣሪያ ምላሽ መስጠቱ፣ የመንግሥትን አምባገነናዊ ሥርዓት የሚጠቁም ነው ብሏል፡፡ ስለዚህም ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች እንደ ጉዳቱ መጠን ካሳ እንዲከፍል፣ ድርጊቱን በፈጸሙ የፀጥታ ኃይሎች ላይ በአስቸኳይ ተጣርቶ ሕጋዊ ዕርምጃ እንዲወሰድ ጠይቋል፡፡ መንግሥት ሰላማዊ ውይይቶችንና ሕዝባዊ ስብሰባዎችን ማበረታታት ሲገባው፣ ይህ ካልሆነ የዘንድሮ ምርጫ ጥያቄ ውስጥ ይገባል ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) በበኩሉ ተቃውሞ ባሰሙ ዜጎች ላይ የተፈጸመው ጥቃት የአምባገነናዊ አገዛዝ ነፀብራቅ ነው በማለት መግለጫ አውጥቷል፡፡ በባህር ዳር ከተማ ነዋሪ በሆኑ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች ላይ የተወሰደው ጭካኔ የሞላበት የኃይል ዕርምጃን በጥብቅ አወግዛለሁ ብሏል፡፡ ቀደም ሲል በሌሎች ሃይማኖቶች ተከታይ በሆኑና በተለያዩ አካባቢዎች በሚኖሩ ዜጎች ላይ ድርጊቱ በተደጋጋሚ ሲፈጸም የቆየ መሆኑን መድረክ ባወጣው መግለጫ አስታውቆ፣ ይህም የሥርዓቱን ኃላፊነት የጎደለው አምባገነናዊ ባህሪ ገላጭና ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው ነው ብሏል፡፡ ለደረሰው ጉዳት ኢሕአዴግ ኃላፊነት ወስዶ በአስቸኳይ ካሳ እንዲከፍልና ጥቃቱን የፈጸሙ ደግሞ ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠይቋል፡፡

No comments:

Post a Comment