እንደ መነሻ
ከሁለት ወር በፊት አንድነትን እንዲመሩ በጠቅላላ ጉባዔ የተመረጡት ኢ/ር ግዛቸው ሺፈራው ጥቅምት ሁለት ቀን 2007 ዓ.ም ካቢኔያቸውን በትነው ስልጣናቸውን በፈቃዳቸው ለብሔራዊ ምክር ቤቱ አስረከቡ፡፡ የቀድሞው ፕሬዘዳንት ኢ/ር ግዛቸው ለምክር ቤቱ ባሰሙት ንግግር በአመራራቸው ያልተደሰቱ በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎችን የ‹‹ልቀቅ›› ጫና መቋቋም እንዳልቻሉና ከህሊናቸው ጋር ተማክረው ለፓርቲው ጥቅም ሲባል በፈቃዳቸው ሃላፊነታቸውን ለመልቀቅ እንደወሰኑ ተናገሩ፡፡
ምክርቤቱም በጥሞና አድምጧቸው ሲያበቃ ውሳኔያቸውን በአድናቆትና አክብሮት በመቀበል በክብር ሸኛቸው፡፡ በጉዳዩ ላይም ጊዜ ወስዶ መከረ፡፡ አንድነትን ያለመሪ ለአንድ ቀንም ቢሆን ማሳደር አደገኛ እንደሆነና የፕሬዘዳንት ምርጫውን ማከናወን እንደሚገባም ወሰነ፡፡ ይህንን ለመወሰን የሚያስችል ስልጣን እንዳለው ከደንቡ ተጠቀሰ፡፡ ‹‹ብሔራዊ ም/ቤቱ ደንብ ከማሻሻል ውጭ ጠቅላላ ጉባዔውን ወክሎ እንዲንቀሳቀስ ውክልና ተሰጥቶታል›› ይላል፡፡ በዚህ የጠቅላላ ጉባዔ ውክልናው መሰረት ሦስት ዕጩ ፕሬዘዳንቶችን በጠቅላላ ጉባዔው የማወዳደሪያ መስፈርት መሰረት አወዳድሮ አቶ በላይ ፈቃዱን የፓቲው ፕሬዘዳንት አደርጎ ሾመ፡፡ ካቢኔያቸውን በአስቸኳይ አዋቅረው ወደ ስራ እንዲገቡ መመሪያ አስተላለፈ፡፡
ትንሽዋ ግርግር
በዚህ ሂደትም ‹‹አልተደሰትንም፣ ኢ/ር ግዛቸው ለምን ሄደብን!›› ያሉ ጥቂት ግለሰቦች ምክር ቤቱ ባካሄደው ምርጫ አምነው ከተሳተፉ በኋላ ሌላ የጎንዮሽ እንቅስቃሴ ያዙ፡፡ ይሄ እንቅስቃሴያቸውም መኢቲቪ፣ ምርጫ ቦርድና በትርፍ ፈላጊ ሃይሎች መታጀብ ጀመረ፡፡ እውነት መጥራቷ ላይቀር መንሻፈፍ ጀመረች፡፡ መግለጫዎች ተዥጎደጎዱ፡፡ የገዥው ፓርቲ ቀኝ እጅ ኢቲቪም ታይቶ በማይታወቅ መልኩ በየቀኑ ከስድስት ጊዜ በላይ በማስተላለፍ ትንሽዋ ግርግር ህይወት እንዲኖራት ጣረ፡፡ ነገርግን እውነቱ እንደዚያ አልነበረምና ግርግርዋ የአንድ ሳምንት ከመሆን አልዘለለችም፡፡ አዲሱ አመራር በስራ በመጠመዱ እና ለጓዳ ወሬዎች ምላሽ ባለመስጠቱ የአባላትን ትኩረትና ድጋፍ ለማግኘት ቻለ፡፡ ግርግሯም ከምሱሩ እንከሸፈ ጥይት ቱሽሽሽሽ አለች፡፡
ምርጫ ቦርድ ግን ምክርቤቱ የመረጠውን አመራር ዕውቅና ለመንፈግ አንገራገረ፡፡ በተደረጉ የደብዳቤ ልውውጦችም ምርጫ ቦርድ ሁሉንም ነገር ተቀብሎ ሲያበቃ አንዲት ትንሽ ቀዳዳ አመጣ፡፡ እሷም፡- ‹‹የጠቅላላ ጉባዔተኛ ኮረም ቁጥር በደንቡ ይካተት›› የምትል ናት፡፡ በተፈለገ ጊዜ ለመምዘዝ የታሰበች ቀይ ካርድ ናት፡፡ ደንብ ሊያሻሽል የሚችለው ደግሞ ጠቅላላ ጉባዔው ነው፡፡ ወደ ተሟሟቀ ህዝባዊ ንቅናቄ ስንገባ ይችን ካርድ ለመጠቀም እንዳሰቡ ግልፅ ነው፡፡ ምርጫ ቦርድ በተወሰኑ ፓርቲዎች ላይ እንደሚያደርገው ጥብቅ ቁጥጥር 60 እና 70 በሚላቸው ፓርቲዎች ላይ ማድረግ ቢችል የፓርቲዎቻችን ቁጥር ከ5 ሊዘል እንደማይችል እርግጠኛ ነኝ፡፡ ስለዚህ አንድነት የምርጫ ቦርድን የመጫወቻ ካርድ ማስጣል እንደሚገባ አመነ፡፡ ጠቅላላ ጉባዔውን መጥራት ለእንደ አንድነት ያለ ሀገራቀፍ መዋቅር ላለው ፓርቲ ብዙ ከባድ አይደለም፡፡ ሆኖም አያውቅም፡፡ እንዴውም በዚህ ወቅት በመላ ሀገሪቱ ያሉ አመራሮችን ማግኘት በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ይሉት አይነት ነው፡፡
ጉባዔው
ጉባዔ ለማካሄድ ቀን ተቆረጠ፡፡ ያለችው አንድ ሳምንት ብቻ ነበረች፡፡ በሀገር ውስጥ ያለው አመራርና አባላት እንዲሁም በውጭ ያሉ ብርቱ ደጋፊዎቻችን ተረባረቡ፡፡ ለጠቅላላ ጉባዔ አባላት ጥሪ ተላለፈ፡፡ የዞንና የወረዳ አመራሮች ጉዳዩን በንቃት ይከታተሉት ነበርና ሆ ብለው አዲስ አበባ ገቡ፡፡ ህወሃት/ኢህአዴግን ያስደነገጠ ጉባዔ ነበር፡፡ በአንድ ሳምንት እንደዚህ የደመቀ ጉባዔ ማካሄድ ብር ለሚነሰንሰው ገዥ ፓርቲ እንጅ ለተቃዋሚዎች የሚቻል አይመስልም፡፡ ለዚህም ‹‹ጉባዔ ጥሩ!›› እንደማስፈራሪያ ያገለግላል፡፡ አንድነት ግን በሀገራቀፍ ደረጃ ያለውን አቅም አሳየ፡፡
አርብ በማለዳው ከ400 በላይ የሚሆነው የጠቅላላ ጉባዔ ተሳታፊ በኢትዮጵያችን ባንዲራ በተመሰለ አለባበስ አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ለብሶ አዳራሹን ሞልቶታል፡፡ ሁሉም ላይ እልህና ወኔ ይነበባል፡፡ ስብሰባው የተጠራበት አጀንዳ ለውይይት ክፍት ሆነ፡፡ ትንሽዋን ግርግር ለመፍጠር የሞከሩ ግለሰቦች ጉባዔተኛው ፊት እንዲከራከሩ ወይም ሂሳቸውን እንዲሰለቅጡ ጥሪ ቢደረግላቸውም ሳይመጡ ቀሩ፡፡ የተገኙ ግለሰቦችም እንደ አሮጌ ቴፕ እየተንተፋተፉ ለምን ወደ ኢቲቪ እንደሄዱ ለማቅረብ ቢሞክሩም ከውግዘት በስተቀር ምላሽ አጡ፡፡ ምክንያቱም ኢቲቪ ለተቃዋሚው ያለው ምልከታ ይታወቅ ነበርና አኮረፍን ብለው ወደ ኢቲቪ መሄዳቸው ክስረት ነበር፡፡
እነሆ ጠቅላላ ጉባዔው ምክር ቤቱ የወሰደው ርምጃ ጠቅላላ ጉባዔው በሰጠው ውክልና መሰረት በመሆኑ ደንባዊም ተገቢም ነው ሲል ወሰነ፡፡ በላይ ፈቃዱም ፓርቲውን እስከ ቀጣይ ጉባኤ ድረስ የፓርቲው ፕሬዘዳንት በመሆን እንዲመራ በማለት በከፍተኛ ድምፅ ወሰነ፡፡ የሚገርመው ከራሱ ከበላይ የቀረበውንና ሌሎች አመራሮች የደገፉትን ዕጩዎች ቀርበው ፕሬዘዳንት ይመረጥ የሚል ሃሳብ ጠቅላላ ጉባኤው ውድቅ በማድረግ የም/ቤቱ ውሳኔ ትክክል ነው በማለት በሙሉ ድምፅ መወሰኑ ነው፡፡
ይሄው ግዙፍ የአንድነት የፖለቲካ ሃይል ደንቡንም አሻሽሏል፡፡ ሌሎች የፖለቲካ ውሳኔዎችንም አሳልፏል፡፡ አንድነት በ2007 ዓ.ም ሀገራቀፍ ምርጫ አሸናፊ ሃይል ሆኖ እንዲወጣ በሚያስችሉት ጉዳዮች ላይ ጥናቶች ቀርበው ውይይት አድርጓል፡፡ ህዝቡን ያሳተፈ ህዝባዊ ንቅናቄ እንዲደረግ እና ምርጫውን ነፃና ፍትሃዊ ለማድረግ ትግሉ ተፋፍሞ እንዲቀጥል ከስምምነት ላይ ደርሷል፡፡
No comments:
Post a Comment