ያሬድ ኃይለማርያም
ከብራስልስ
መስከረም 3 ቀን 2007 ዓ.ም.
በአለም አቀፍ ደረጃ ስለ ሽብርተኝነት ያለው አረዳድ እና ወያኔ ሽብርተኝነትን የሚተረጉምበት መንገድ ለየቅል ናቸው። በአለም አቀፍ ደረጃ የሽብርተኝነት ጉዳይ እንደ ዋና አጀንዳ ተይዞ ለመጀመሪያ ጊዜ መነጋገሪያ የሆነው በ1934 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) ነው። በዛሬው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተተካው የሊግ ኦፍ ኔሽን በሽብርተኝነት ዙሪያ ሲመክር ቆይቶ በ1937 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) ሽብርተኝነትን ለመከላከል እና ለመቅጣት የሚያስችል አንድ ድንጋጌ (Convention for the prevention and punishment of terrorism) አጽድቋል። ከዚህ ድንጋጌም በኋላ ከ14 የሚበልጡ አለም አቀፍ ድንጋጌዎችና ስምምነቶች በተባበሩት መንግስታት ጸድቀዋል። የእነዚህ ሕጎች ዋነኛ አላማም መንግሥታት ሽብርተኝነትን በተናጠልም ሆነ በጋራ እንዲዋጉ ለማስተባበር ብቻ ሳይሆን ሽብርተኝነትን እንዋጋለን በሚል ሽፋን በዜጎቻቸውም ሆነ በተቀረው የሰው ዘር ላይ መድልዎን፣ ግፍና በደሎችን በመፈጸም ሰብአዊ መብቶችን ለማክበርና ለማስከበር የተጣለባቸውን አለም አቀፋዊ ግዴታ እንዳይዘነጉም ለማሳሰብ ነው። ምንም እንኳን ኃያላኖቹ አገራት ሳይቀሩ የጸረ-ሽብር ዘመቻን ለፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞቻቸው ማስገኛ ሲያውሉትና ሲመነዝሩት በግልጽ ቢስተዋልም በሽብርተኝነት ላይ ያላቸው ምልከታና አቋም ግን በአለም አቀፍ ደረጃ ከተቀመጡት መመዘኛዎች የራቁ አይደሉም።
በወያኔ መንደር ሽብርተኝነት ለየት ያለ መልክ ነው ያለው። የወያኔ የሽብርተኝነት መስፈርትም ሆነ ትርጓሜ ብዙ ሃገሮች፤ አንባገነን የተባሉት ሳይቀሩ ስለሽብርተኝነት ካላቸው ግንዛቤም ሆነ ከአለም አቀፉ መመዘኛዎች የተለየ ነው። የሽብርተኝነት ተግባር እየተተረጎመ ያለው በወያኔ ባልሥልጣናት የመሸበር መንፈስና ሰለራሳቸው ሥልጣን ብቻ በማሰብ ከጭንቀት በመነጨ የፍርሃት ስሜት ላይ የተመሰረተ ነው:: ባለሥልጣናቱን ጭንቅት ወስጥ የሚጥል፣ የሚያስደነብር፣ የሚያስቀይም፣ የሚያስቆጣ ወይም የሚያሰፈራራና እንቅልፍ አጥተው እንዲያድሩ የሚያደርግ ተግባራትን የፈጸመ ሁሉ በሽብርተኛነት ይፈረጃል:: ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ቀይ መስመር አስምረውና አዋቅረውት የሄዱትን የወያኔን አጥር የሚነቀንቅ ብቻ ሳይሆን ጠጋ የሚልም ሁሉ በአሸባሪነተ ሊፈረጅ፣ ሊታሰርና ሊከሰስ እንዲሁም ሊፈረድበት እንደሚችል እየታየ ነው:: ለአገዛዝ ሥርዓቱ የሥልጣን ዘመን መራዘም ስጋት ሊሆኑ ይችላሉ የሚሉዋቸውን አካላትና ግልሰቦች ሁሉ አሸባሪ አያሉ መክሰስ የተለመደ ሆኗል። ብዕራቸውን አንስተው በመንግሥት ላይ የሰሉ ትችቶችን በመጻፍ ተቃውሟቸውን የገለጹ፣ የሃይማኖትና የተለያዩ ማህበራዊ ተቋማትን በመወከል የመብት ጥያቄዎችን አንስተው የተሟገቱ የሕዝብ ወኪሎች፣ በወያኔ በባለሥልጣናት የተፈጸሙ ወንጀሎችን፣ ሙስናዎችን፣ አገርና ሕዝብን ያዋረዱ ተግባራትን ያጋለጡና ባደባባይ ሥርዓቱን የሞገቱ ጋዜጠኞች፣ የማህብራዊ ድረ-ገጽ ገተሳታፊዎች፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፣ በሕጋዊ መንገድ ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላትን ጭምር የሽብርተኝነት ካባ እያከናነቡ ማጎርና መወንጀል የሥርዓቱ ዋና ስልት ሆኗል። ይህም ወያኔ አለም በሚሸበርበት ጉዳይ ሳይሆን ራሱ በፍርሃት በፈጠረው የሽብር ዓለም ወሰጥ መሆኑን ያሳያል::
ከግለሰብ (ከሟቹ ጠ/ሚ መለስ) አንባገነናዊነት ወደ ቡድን አንባገነናዊነት የተሸጋገረው የወያኔ-ኢሕአዴግ ሥርዓት ከመቼው ጊዜ በከፋ ሁኔታ በፍርሃት መዋጡን የሚያመላክቱ በርካታ ክስተቶችንም እያስተዋልን ነው። ፍጹም አምባገነንና ፈላጭ ቆራጭ የነበሩትን አቶ መለስ በብዙ ትናንሽ መለሶች ለመተካት ተጥሯል። ምንም እንኳን በበቂ ማስረጃ ማረጋገጥ ባይቻልም የሥርዓቱ ተዋናይ ከነበሩ እና አሁንም በሥልጣን ላይ ካሉ የአመራር አባላት እየሾለኩ የሚወጡት መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በድርጅቱ ውስጥ ባሉት ጎሣን መሰረት ያደረጉት ክፍልፋዮች መካከል ከሚስተዋለው ጤናማ ያልሆነ የፖለቲካ ፉክክር እና ሽኩቻ ባሻገር በግለሰቦች ዙሪያ የመቧደን ስሜት እየጎላ በመምጣቱም ድርጅቱ ውስጥ ፍርሃት እንዲነግስ አድርጓል። ይህንን ክፍተት በመጠቀም በሰላማዊም ሆነ በነፍጥ ኃይል የሥርዓት ለውጥ ለማምጣት የተደራጁ የፖለቲካ ኃይሎችና ቡድኖች መነቃቃትም በፍርሃት ውስጥ ያለውን የወያኔን ሥርዓት የበለጠ እንዲደነብር አድርጎታል።
በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሰላማዊ ትግል አምነው ከተደራጁት የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል የተወሰኑት በተከታታይ ያካሄዷቸው የተቃውሞ ሰልፎችና የሕዝብ ምላሽ፣ አፈና እና ስቃዩን ተቋቁሞ ለአመታት የዘለቀው የሙስሊሙ ማኅበረሰብ እንቅስቃሴ፣ ልማትን ሽፋን አድርጎ ሥር እየሰደደ ያለው የኑሮ ዋስትና መታጣትና የከፋ ድህነት፣ በሃያ አመት ውስጥ የተዘራው የዘር ፖለቲካና በአዲሱ ትውልድ አእምሮ ውስጥ ፍሬውን አፍርቶ በሥርዓቱ ላይ ጭምር የዘር ጥላቸቻን ማሳየቱ እና ሌሎችም ውጫዊ ምክንያቶች ተደማምረው ገዢውን ኃይል እንዲፈራና የፈሪ ዱላውንም እንዲያነሳ አስገድደውታል። ዛሬ የወያኔ አመራሮች ሕዝብን ብቻ ሳይሆን የሚፈሩት እራሳቸውንም ጭምር ነው። ድርጅቱ አባላቱን ይፈራል፣ በአወራውና አጃቢ ድርጅቶች መካከል መፈራራት አለ፣ አባላቱ እርስ በርስ ይፈራራሉ፣ አባላቱ መሪዎቻቸውን ይፈራሉ፣ መሪዎች ተከታዮቻቸውን (ተራ ካድሬውን) ይፈራሉ፣ በአመራር ላይ ያሉት ሰዎችም እርስ በርስ ይፈራራሉ። የአንድ ላምስት የስለላ መዋቅር ምንጩም ይህ ነው። አንድ ሥርዓት ጭልጥ ወዳለ አንባገነናዊነት (totalitarianism) ሲገባ ሕዝብን ብቻ ሳይሆን እራሱንም ይፈራል:: በደርግ ዘመንም የሆነው የሄው ነበር:: ለዚህም ነው በእንዲህ ያሉ ሥርዓቶች ውስጥ አባላቱና ደጋፊዎች ከሚሰሩበት ይልቅ እርስ በርስ የሚገማገሙበት ጊዜ ሳይበልጥ አይቀርም የሚባለው። ሕዝብን እና ራስን መፍራት የሽብር መንፈስ ውስጥ ይከታል።
የፖለቲካ ተቀናቃኞችንና የሰላ ትችት የሚሰነዝሩበትን ሁሉ አሸባሪ እያሉ የጥቃት ዒላማ ማድረጉም ዋነኛ አላማው አነሱን ከትግሉ ሜዳ ለማሸሽ ብቻ ሳይሆን የቀረውንም ሕዝብ ለማሸማቀቅና በፍርሃተ ውስጥ ሆኖ ጸጥ ለጥ ብሎ እንዲገዛም ለማድረግ ነው:: ሥርዓቱ የሕዝብ ስላልሆነ ሕዝብን ይፈራል። ለነገሩ ሕዝብን ብቻ ሳይሆን ለጥቅም ሲሉ በዙሪያው የተኮለኮሉትን ሹማምንት፣ አባላቱን እና ‘የአባቴ ቤት ሲዘረፍ አብሬ ልዝረፍ’ በሚል ሕሊና ማጣት ወይም አይን ያወጣ ሌብነት የከበቡትን ‘መሁራን’ና ባለሃበቶች ጭምር ይፈራል:: በመሆኑም የሥርዓቱ ደጋፊዎችና አባላቱ ከሌላው የህብረተሰብ ክፍል በከፋ ሁኔታ የአፈና መዋቀሩ ዋነኛ ሰለቦች ናቸው:: አንድ የወያኔ-ኢህአዴግ አባል የሆነ ሰው በአባልነቱ የተለያዩ ቁሳዊ ጥቅሞችን በብቸኝነት ወይም በቅድሚያ ከሌላው ሰው ተለይቶ የማግኘት እድል ይኖረዋል:: ይሁን እንጂ ይህ እድል በነጻነት ማሰብን፣ ሃሳቡን በነጻነት መግለጽን፣ ያመነበትን የፖለቲካም ሆነ ሌሎች አስተሳሰቦቹን ባደባባይ ማንጸባረቅን ወይም ባመነበት ጉዳይ አቋም የመያዝን፣ በመንግሥት ፖሊሲዎችና አፈጻጸሞች ላይ የሰሉ ትችቶችን የመሰንዘር ባጠቃላይ የፖለቲካና የሲቪል መብቶቹንና ነጻነቶቹን አያጎናጽፈውም:: በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ያሉ ሰዎች የነጻነትን ጣእም አያቁትም።
ጥልቅ በሆነ ፍርሃት ወስጥ ሆኖና ውሉ በማይታወቅ የሸብር ስጋት ተሸብሮ ሕዝብን ማሸበር፣ በጎሣ ፖለቲካ የሰበጣጠሩትን ሕዝብ የቡና ማህበር ድረስ ሥር የሰደደ የአፈና መዋቅር ዘርግቶ በመጠርነፍ የልቡን እንኳን ቡና እየጠጣ እንዳይተነፍስና በሌሎች ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቹም እንዳይተዛዘንና እንዳይረዳዳ ማድረግ ሥርዓቱ አገሪቱን እና ሕዝቡን ይዞ ሊገባ እየተንደረደረ ያለበትን ጥልቅ ገደል ያመላከታል:: በቅርቡ የኦሮሚያ ክልል ተማሪዎች ያነሱዋቸው ጥያቄዎች ባህሪያት እና የሥርዓቱ ምላሽ የዚህን አደጋ ቅርበት ጥሩ አድርጎ ያሳያል:: እንግዲህ የሁሉም ሰው ጥያቄ እንዲህ ፈርቶ እያስፈራራ፣ ተሸብሮ እያሸበረ፣ ሕዝብንም አገልጋዮቹንም አፍኖ አገሬውን ሁሉ የቁም እስረኛ፤ ቀሪውንም በየማጎሪያው ካምፑ ከርችሞ እያሰቃየ ያለውን ክፉና በአጉል ቀን የተጣባንን ሥርዓት በምን መላና ዘዴ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከትከሻችን ላይ አውርደን እንገላገለው የሚል ይመስለኛል:: ለዚህ ጥያቄ መልስ ማግኘት እንዲህ ቀላል ባይሆንም ወደ መልሱ የሚያመሩ መንገዶችን ግን መጠቆም ይቻል ይሆናል::
እኛስ?
ሥርዓቱ ዕለት ተዕለት በአገርና በሕዝብ ላይ የሚፈጽማቸውን ወንጀሎችና ደባዎች፤ እንዲሁም የሰብአዊ መብት ረገጣዎች እየተከታተሉ በማጋለጥና ሕዝብ እንዲያውቀው በማደረግ ረገድ የግል ሚዲያውና የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ትልቁን ሚና ተጫውተዋል:: ይሁንና ጥረታቸውን የሚያግዝና ሥርዓቱን ሊያርቅ የሚችል ሌላ የተጠናከራና አገራዊ ዕራይ ያነገበ ኃይል ሊፈጠር ወይም ከተፈጠረም በዘላቂነት ሊቆይ ባለመቻሉ የተቆለሉት ወንጀሎችና ጥፋቶች የወያኔን ገጽታ ወደ አስፈሪ ጭራቅነት አግዝፈውታል:: በተቃዋሚ ጎራ ውስጥ ያሉ ቡዙዎቹ የውይይት መድረኮችና ሚዲያዎች ወያኔን ለማዋረድ በማሰብ ብቻ በየቀኑ የሚያዥጎደጉዱት ፕሮፓጋንዳ ብዙዎች ወያኔን የማይደፈር ኃይል አድርገው እንዲያስቡት እስተዋጾ አድርጓል:: ከዚያም በላይ ከጥላቻ ያልዘለለው የአንዳንድ ሚዲያዎች ያላቋረጠ የጸረ-ወያኔ ፕሮፓጋንዳ ተደማምሮ ደርግ አላሸቆት የሄደውን የሕዝብ ወኔና የመንፈስ ጥንካሬ እንዳያገግምና የፖለቲካ ምህዳሩን እንደ ፈንጂ ቀጠና እንዲያየው አድርጎታል:: ወያኔ ባያወቀው ነው እንጂ እነዚህን ሚዲያዎች ለማፈንና ከሕዝብ ዘንድ እንዳይደርሱ ለማድረግ የሚጥረው እነዚህ ሚዲያዎች ባለውለተኞቹ ናቸው:: በግምት 95% በሚሆነው ዘገባቸው የወያኔን ወንጀል የመፈጸም ችሎታ፣ አቅምና የአፈጻጸም ሥልቱን፣ ስለ ተደራጀው የአፈና መዋቀሩ፣ ወደር ስለሌለው ጭካኔው፣ ከሕግ በላይ ሰለመሆኑ እና ያሻውን ቢያደርግ የሚመልሰው አንዳችም ኃይል አለመኖሩን ነው ነጋ ጠባ የሚዘከዝኩት:: ወያኔ እነኚህን መድረኮች ከሚያፍናቸው ይልቅ ሕዝብን የማስፈራራቱን ሥራ እየሰሩለት ስለሆነ በእጅ አዙርም ቢሆን ገንዘብ እየደጎመ ቢያጠናክራቸው አድሜውን ለማራዘም ይረዱታል::
በእነዚህ መድረኮች እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ስላለው እምቅ ኃይል፣ በሰውነቱ ሰለተጎናጸፋቸው መበቶችና ነጻነቶች፣ ከሌሎች ጋር በጋራ አብሮ ሲቆም ሊፈጥር ስለሚችለው ኃያል ጉልበትና ተአምር፣ ሕዝብ እንዴት የሥልጣን ባለቤትነቱን ማረጋገጥ እንደሚችል፣ የሰላማዊ እመቢተኝነት ኃያልነትን ማወራትና ማሰተማር የተለመደ አይደለም:: ወያኔን ለመታገል በተቃራኒው ተደራጅቶ ሰለቆመውም የፖለቲካ ኃይል ከሚናገሩት ውስጥ አመዛኙ መርዶ ነው:: አንጃ ተፈጠረ፣ ኅብረት ፈረሰ፣ ውህደቱ መከነ፣ እገሌ ከዳ፣ እገሌ የተባለው ፓርቲ ‘እገሌ-ዲ’ የተባላ ደባል አፈራ የሚሉና አዳዲስ ግንባሮችና ውጥኖች መጠንሰሳቸውን ሰምቶ የሚቦርቀው ሰው ላቡን ሳያደርቅ ደም እንባ የሚያስለቅሱ የክሸፈት መርዶዎችን ያበስሩናል:: እንደ እኔ እምነት እነዚህ ሚዲያዎችም ሆኑ የሚዲያዎቹ ተሳታፊዎች የሳቱት ትልቁ ነገር የኢትዮጵያ ሕዝብ ዝምታ የወያኔን ደባና ወንጀል በደንብ ካለማወቅ ነው ከሚል መነሻ ላይ ሆነው ሥራቸውን መጀመራቸው ይመስለኛል:: ተደበደብክ፣ ታሰርክ፣ ታፈንክ፣ በላይህ ላይ ሞሰኑብህ እያሉ ለተደበዳቢው፣ ለታፋኙ፣ ለታሳሪው፣ ሌት ከቀን የግፍ እንቆቆውን ለሚጋተው ሰው ለራሱ ‘ሰበር’ ዜና እያሉ ማደንቆር ተበዳዩን አያጀግነውም፣ ለትግልም አያነሳሳውም፣ ብርታትም ሊሆነው አይችልም:: የማይካደው ቁምነገር ግን ቢያንስ በደሌን ሕዝብ አውቆልኛል ብሎ አንዲጽናና እና አሱም የሌሎችን በደል እያደመጠ በደልን እንዲላመድ ይረዳው ይሆናል:: ለዛም የምስለኛል ይህ ሁሉ መከራ ቢሚወርድበት አገር ከ90 ሚሊዮን ሕዝብ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ብቻ ለራሳቸውና ለሕዝብ ነጻነትና ከብር ባደባባይ ወጥተው የሚታገሉት:: ለዚህም ይመስለኛል ሃዲዱን የሳተውን የአገሪቱን የፖለቲካ አቅጣጫ ለማስተካከልና መረን የለቀቀውን የወያኔን ባህሪ ለማረቅ ዕዳው በጣት በሚቆጠሩ ግለሰቦችና ደርጅቶች ላይ የተጫነው:: እዚህ ላይ ለማሳሰብ የምወደው ሥርዓቱ የሚፈጽማቸው ወንጀሎችና ጠፋቶች አይነገሩ፣ ሕዝብ እንዳይሸበር ተሸፋፍነው ይቅሩ እያልኩ አይደለም::
ሕዝቡ የሚደርስበትን በደል ጠንቅቆ ሰለሚያወቅ እሱኑ ነጋ ጠባ አያወጡና እያወረዱ ማብጠልጠል መፍትሄ አይሆንም:: ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማህበራት፣ ጋዜጠኞችም ሆኑ ሌሎች የለውጥ ኃይሎች በሕዝቡ ውስጥ የሰረጸውን ጨለምተኝነት ለመግፈፍና ሕዝቡም የትግሉ አካል እንዲሆን፤ እንዲሁም የአገሬ ጉዳይ ያገባኛል፣ ባለድርሻም ነኝ፣ ኃላፊነትም አለብኝ፣ ለውጥ ለማምጣትም የሚያስችል አቅም አለኝ በሎ ማሰብ እንዲጀምር ሊያስተምሩትና አቅሙን አጉልተው ሊያሳዩት ይገባል:: መልካም ዜጋን የመገንባት ሥራ ላይ ልናተኩር ይገባል:: የአገዛዝ ሥርዓቱን አያገዘፉ ሕዝብን ማኮሰስና ማስፈራራት ወያኔ እንደተፈራ ሌሎች አስርት ዓመታትን እንዲቆይ ይረዳዋል:: ሸነጥ ሲያደርገን በቻ እየተነሳን ሥርዓቱን የገለባ ክምር አድርጎ በማቅለል በስድስት ወር እንንደዋለን፣ የመሪዎቹን ጉሮሮ አንቀን ከምድረ ገጽ እናጠፋለን አያሉ መፎከርና ለአመታት ይህንኑ እየደጋገሙ መማልና መገዘት በጭንቅ ውስጥ ያለውን ሕዝብ በቀቢጸ ተሰፋ እንዲቆይና በአገር ላይ የተጋረጠውንም አደጋ በቅጡ እንዳያይ በማድረግ መዘናጋትን ይፈጥራል እንጂ ግዴታውን እንዲወጣ አያነሳሳውም:: ፉከራና ቀረርቶውም እየተስተዋለ ይሁን::
በቸር እንሰንብት!
No comments:
Post a Comment